ኢትዮ ሳት የመገናኛ ብዙሃን ተደራሽነትንና ተጽእኖ ፈጣሪነትን ለማሳደግ ይረዳል

ሰኔ 8፤2009

በኢትዮጵያ የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ያቀፈ አዲስ ሳተላይት/ኢትዮ-ሳት/ ተጀምሯል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እውቅ ከሆኑ አለም አቀፍ ተቋማት ኢቴል ሳትና ሲኤስ ጋር በመሆን የጀመረው ይህ መርሃ ግብር የመገናኛ ብዙሃን ተደራሽነትንና ተጽህኖ ፈጣሪነትን ለማሳደግ እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡

የሀገር ውስጥ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንደ ናይል ሳት ፣አረብ ሳትና መሰል ተቋማት ጋር ኪራይ የሚፈጽሙት በሶስተኛ ወገን በኩል መሆኑ ለተጋነነ ወጪ፣ ለተደራሽነት ውስንነት፤ ለጥራት ችግርና ለተወዳዳሪነታቸው መሰናክል እየሆነባቸው መሆኑ ተነግሯል፡፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ይህ የጀመረው አዲሱ መርዓ-ግብር ይህን ችግር ለመፍታት ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በዚህም መሰረት የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ በሌሎች ሳተላይቶች አብረው መዳበል ሳያስፈልጋቸው ኢትዮ-ሳት በተሰኘው ብሔራዊ የጋራና የተቀናጀ ሳተላይት በመገኘት ለተመልካቹ እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡

ከሁለት ወራት አስቀድሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንና የኦሮሚያ ቲቪን ጨምሮ በ5 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የተጀመረው የኢትዮ-ሳት ስርጭት እየሰፋ መጥቶ የተለያዮ ተቋማት ስምምነት እየፈፀሙም ይገኛሉ፡፡

በሂደትም ሀገሪቷ የራሷን ሳተላይት በማምጠቅ የሳይበር ምህዳሩን የማስፋት ግብም ተቀምጧል፡፡

የኢትዮ-ሳት ፍርኩዊንሲ፦ሳተላይት፡E8WB፣ ፍርኩዊንሲ፡11512፣ FEC= 2/3

በአበበ ባዮ