ሚኒስቴሩ በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ነው- ቋሚ ኮሚቴው

ሰኔ 8፤2009

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 40ኛውን መደበኛ ስብሰባ ባካሄደበት ወቅት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴርን የ2009 ዓ.ም በጀት የ10 ወራት እቅድ አፈጻጸምን አድምጧል፡፡

ሚኒስትሩ ዶ/ር አምባቸው መኮንን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በእድገትና ትራንስፎርሜሽ እቅዱ መሰረት ለበጀት አመቱ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ሶስተኛ የሰራዊት ክንፎችን በማንቀሳቀስ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሁሉም ሰራተኞች በጥልቅ የመታደስ ንቅናቄ ውስጥ እንዲያልፉ መደረጉንና እቅዶቹም በኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በሚያግዝ መልኩ ተቀርጸው ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በዘርፉ ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠርና ገቢን በማሻሻል ድህነትን ለመቀነስ በተሰሩ ስራዎችም 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ያህል ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በከተሞች የሚታየውን የቤት እጥረት ለመቅረፍ የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀሙ እንደሆነና በህብረት ስራ ማህበራት 73 ሺህ 227 ቤቶች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባን ሳይጨምር በክልሎችና በድሬደዋ ከተማ በአጠቃላይ 14 ሺህ 742 ቤቶች ግንባታ ተጠናቋል ነው ያሉት፡፡

መስሪያ ቤቱ ለአመራሮችቹና ፈጻሚ አካላት የሰጠውን መጠነ ሰፊ የአቅም ግንባታ ስራዎችን፤ ጠንካራ የጥልቅ ተሃድሶ መድረክ በማዘጋጀት መነቃቃት እንደፈጠር ማድረጉ በምክር ቤቱ የከተማ ልማትና ቤቶች ቋሚ ኮሜቴው በጠንካራ ጎኑ የተገለጹ ናቸው፡፡

እንደ ደካማ ጎኑ ካነሳቸው ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ መንግስት ለወጣቶች የስራ እድልን ለመፍጣር ካለው ጽኑ ፍላጎት አንጻር የታሰበውን ያህል አላከናወነም ብሏል፡፡

በዳዊት ጣሰው