ከለንደን ህንጻ ቃጠሎ በኋላ 8 ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የደረሱበት አልታወቀም

ሰኔ 10፤2009

በለንደን በጋራ መኖሪያ ህንጻ ደርሶ በነበረው አደጋ በኋላ እካሁን ስምንት ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በህይወት መኖር አለመኖራቸው እንዳልታወቀ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ፡፡

በለንደን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶ/ር ሃይለሚካኤል አበራ ሶስት ተጎጂ ቤተሰቦችን የጎበኙ ሲሆን የተሰማቸውን ሃዘንም ገልጸዋል፡፡

ወደ ፊትም ከዚህ አሰቃቂ ችግር እንዲወጡ ለማድረግ የተቻለውን ድጋፍ ለማበርከት እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ለእንግሊዙ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የሃዘን መግለጫ መላካቸውን ኤምባሲው በድህረገጹ ባሰፈረው መረጃ አብራርቷል፡፡

እስካሁን በአደጋው 30 ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን 24 የሚሆኑት ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነግሯል፡፡

ምንጭ፡ በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ/ውጪ ጉዳይ