የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ተጨማሪ ግብአቶች ሊካተቱበት እንደሚገባ ተገለጸ

ሰኔ 11፤2009

ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለው የፌዴራሊዝም ስርዓት በአገሪቱ  እየተከሰቱ  ያሉ  አንዳንድ ግጭቶችን በሚፈታ  መልኩ ተጨማሪ ግብአቶች  ሊካተቱበት እንደሚገባ አንድ ጥናት አመለከተ።

የፌዴራል ስርዓቱ የፈተናቸው ማነቆዎችና  ያልተሻገራቸው ፈተናዎች በሚል ርዕስ አገር አቀፍ ምክክር ተካሂዷል።

የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ባዘጋጀው አገር አቀፍ የምክክር መድረክ በአገሪቱ እየተተገበረ ያለው የፌዴራሊዝም ስርዓት ፋይዳውና ጉድለቱ በሚል ርዕስ ጥናታዊ  ጽሑፍ ቀርቧል።

በቀረበው ጽሑፍ ላይም ሙሁራን፣ የመንግስት ሀላፊዎችና  ተመራማሪዎች ውይይት አድርገውበታል።

ጥናቱ  ብሔርን መሰረት ያደረገ የፌዴራሊዝም ስርዓትን መከተል እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት ብቸኛ አማራጭ ነው ፥ ነገር ግን ይህ የፌዴራሊዝም ስርዓት በየጊዜው ተጨማሪ ግብአቶች ካልተካተቱበት በጊዜ ሂደት የሚፈጠሩ ፈተናዎችን የማይፈታበት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ያስቀምጣል።

የጉባኤው ተሳታፊዎችም በጥናታዊ ጽሑፉ ዙሪያ ጥያቄና አስተያየት በማቅረብ ምክክር አድርገውበታል።

የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ አገሪቱ የምትከተለውን ፖለቲካዊ ርእዮተ አለም ለውይይት በማቅረብ ንድፈ ሀሳቦቹ  በሳይንሳዊ መንገድ እንዲመሩ ሙሁራን በዘርፉ ጥናት እንዲያደርጉ የሚሰራ አካዳሚ ነው።

ሪፖርተር :-አማረ ተመስገን