ኢትዮጵያ ኤርትራና ጅቡቲ በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት እንዲያረግቡት ጥሪ አቀረበች

ሰኔ 11፤2009

ኢትዮጵያ በኤርትራና በጅቡቲ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት አገራቱ እንዲያረግቡት ጥሪ አቀረበች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢቢሲ በላከው መግለጫ ኢትዮጵያ በሁለቱ አገራት መካከል በዱመሪያ ደሴት ዙሪያ የተከሰተውን ውጥረት ለማርገብ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን እያደረገ ያለውን ጥረት እንደምትደግፍ ገልጻለች።

ኮሚሽኑ በሁለቱ አገራት ድንበር አከባቢዎች መርማሪ ቡድን ለመላክ መወሰኑንም እንደምትደግፍ አስታውቃል።

ኢትዮጵያም ሁለቱ አገራት ውጥረት ከሚያባብሱ ድርጊቶች ተቆጥበው ችግሮችን በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርባለች።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው ውጥረት እልባት እንዲያገኝ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ኢትዮጵያ ጥሪ አቅርባለች።