የአርጆ ደዴሳ የስኳር ፋብሪካ ስራ ማቆሙን ገለጸ

ሰኔ 11፤2009

የአርጆ ደዴሳ የስኳር ፋብሪካ የሀይል አቅርቦት እጥረትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ስራ ማቆሙን ገለጸ።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ፋብሪካው ያጋጠሙትን ችግሮች ተቀርፈው ወደ ስራ እንዲገባ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የአርጆ ደዴሳ የስኳር ፋብሪካ በግብአት እጥረት ካለፉት አራት ወራት ጀምሮ ማምረት ማቆሙን ገልጿል።

የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ካባ መርጋ ፋብሪካው በሸንኮራ አገዳ እጦት፣ በኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥ እና በካሳ ክፍያ ችግር ምክንያት ምርት ማምረት ማቆሙን ተናግረዋል።

የሸንኮራ አገዳ እጦት በምክንያትነት የተጠቀሰው በደዴሳ ወንዝ ላይ ለዚሁ አላማ እየተገነባ ያለው ግድብ በጊዜ አለመጠናቀቁ እና ከግድቡ ወደ ሸንኮራ አገዳ እርሻ የሚሄደው ቱቦ ስራ በመጓተቱ እንደሆነም ገልጸዋል።

የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የአርጆ  ደዴሳ ስኳር ፋብሪካ በምርት ጥራቱና በአመራረት ሂደቱ በኢትዮጵያ ካሉ ፋብሪካዎች የተለየ መሆኑን ገልጸው ፋብሪካው የተደቀኑበት የተለያዩ ችግሮች በሙሉ አቅሙ እንዳይሰራ አድርገውታል ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ፋብሪካው የገጠሙትን ችግሮች በመፍታት በሙሉ አቅሙ እንዲያመርት መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

ፋብሪካው ከ2ሺህ 500 ቋሚና ጊዜያው ሰራተኞች አሉት።

ሪፖርተ:- ሰሎሞን ጸጋዬ (ከነቀምቴ)