የወጣቶች የጤና ችግሮችን ለመፍታት የአህጉሪቱ የትምህርት ስርዓቱ እንዲሻሻል ጥሪ ቀረበ

ሰኔ 27፣2009

የአፍሪካን የወጣቶች የጤና ችግሮች ለመፍታት የአህጉሪቱ የትምህርት ስርዓት እንዲሻሻል የአፍሪካ ቀዳማዊት እመቤቶች ጥምረት ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ የወጣቶችን ተጠቃሚነት በማሳደግ አፍሪካ ከወጣቶቿ መጠቀም ይኖርባታል ብለዋል።

19ኛው የቀዳማዊት እመቤቶች ጥምረት ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ባለፉት አስር ዓመታት የተላላፊ  በሽታዎች መቀነስ እፎይታን የሰጣት አፍሪካ  የታዳጊ  ወጣቶች ያልጠነከረ  የስነ ጾታ  ባህሪይ ያሰጋታል ተብሏል።

በኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ አተኩሮ የተጀመረው የአፍሪካ የቀዳማዊት እመቤቶች ጥምረትም አሁን ላይ ትኩረቱን በታዳጊዎች ጤና ላይ አድርጋል።

የጋና ቀዳማዊት እመቤት ሬቤካ አኩሞ አዶ በአብዛኛው የአፍሪካ ወጣቶች በጤና ጉዳዮቻቸው ላይ ትኩረታቸው መቀነሱን ገልጸው አመቺ የሆነ የጤና አገልግሎትም እያገኙም ብለዋል።

ቀዳማዊት እመቤቷ ይህም በግብረ ስጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ሳንገነዘባቸው እንዲስፋፉ ያደርጋል ነው ያሉት።

ጥምረቱ በአዲስ አበባ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የጤና አጠባበቅ እንዲስተካከል በዋናነት የትምህርት ስርዓቶች መሻሻል አለባቸው ብሏል።

በጉባኤው ትምህርት ታዳጊዎችን ጤናቸውን እንዲጠብቁ እና ላቅ ያለ ግንዛቤ  እንዲኖራቸው ያደርጋል፣ በጾታዊ ግንኙነታቸው ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያግዛቸዋልም ተብሏል።

በተለይም ዋና ተጠቂ የሆኑት የሴቶችን ተጋላጭነት ለመቀነስ በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ ለውጥ መምጣት እንዳለበትም ተገልጿል።

የጥምረቱ ትኩረት ከአፍሪካ  ሕብረት የማሕበራዊ  ጉዳዮች ኮሚሽን፣ ከዓለም የጤና ድርጅት እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፉን አግኝቷል።

ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በኢትዮጵያ ፖሊሲዎች ድጋፍ ያለው የጥምረቱ እቅድ አፈጻጸም ጠንካራ እንዲሆን ተጽእኖ እናሳድራለን ብለዋል።

ሪፖርተር:-ተአምርአየሁ ወንድማገኝ