አፍሪካውያን የውስጥ ቱሪዝማቸውን እንዲያሳድጉ ተ.መ.ድ ጠየቀ

ሰኔ29፤2009

የአፍሪካ መሪዎች የውስጥና አህጉራዊ ቱሪዝምን ለማሳደግ ትኩረት አድርገው መስራት እንደሚጠበቅባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ2017 የአፍሪካ ምጣኔ ሀብት ልማትን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርቱ የአህጉሪቱ የውስጥ ቱሪዝም ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት እያሳየ እንደመጣና አገራቱም ቱሪዝም ለምጣኔ ሀብት ያለውን ከፍተኛ እምቅ አቅም መቀበላቸውን አትቷል፡፡

በአህጉሪቱ ነፃ የንግድ ቀጠና ለመፍጠር እየተደረገ ባለው ጥረት ውስጥ መንግስታት የቱሪዝም ጉዳይ በአገልግሎት ዘርፍ ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም የሚያስገኝ በመሆኑ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የያዝነውን የፈረንጆች አመት "ዘላቂ ቱሪዝም ለልማት" በሚል ሰይሞታል፡፡

ቱሪዝም በአፍሪካ እያበበ የሚገኝ ኢንዱስትሪ ሲሆን ከ21 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የስራ እድል ምክንያትም ሆኗል፡፡

የአፍሪካ አገራት የድንበር ተሻጋሪ የትራንስፖት ዘርፉን ለማሳደግ ቢሰራ እንዲሁም ነፃ ዝውውር ቢፈጠር ቱሪዝሙን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚቻልም ነው በሪፖርቱ የተገለፀው፡፡

አፍሪን ከሚጎበኙ 10 ቱሪስቶች አራቱ ከዚሁ ከአህጉሪቱ የሚመጡ ሲሆን ከሰሀራ በታች ባሉ አገራት ደግሞ ከ3 ቱሪስቶች ሁለቱ አፍሪካውያን እንደሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ምንጭ፡- ሺንዋ