ስዊዲን በግብርናና በትምህርት ዘርፍ ላይ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች

ሐምሌ 04፤2009

ስዊዲን በግብርናና በትምህርት ዘርፍ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች፡፡

ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በኢትዮጵያ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የስዊዲን አምባሳደር ጃን ሣዴክን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ በርካታ የስዊድን ባለሀብቶች መጥተው መሥራት እንደሚችሉና ወደፊትም ይህ ሁኔታ ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል፡፡

አምባሳደር  ጃን ሣዴክ በበኩላቸው እንደ ኤች ኤምና ኤሪክሰን የመሳሰሉ ታላላቅ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡

ስዊዲን የኢትዮጵያን ቡና ወደ ሀገሯ በማስገባት ከዓለም 2ኛ ናት ያሉት አምባሳደር ጃን ሣዴክ በቀጣይም በቡና እና በአበባ ምርት የሀገራቱን የንግድ እንቅስቃሴ ይበልጥ ማሳደግ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

የስዊዲን መንግሥት በኢትዮጵያ ያለውን አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴ ለመደገፍ የሚያስችል የ1 ቢሊዮን የስዊድን ገንዘብ መፍቀዱንም ተናግረዋል፡፡

ተሳናባቹ አምባሳደር ጃን ሣዴክ በኢትዮጵያ ያሳለፏቸው 4 የሥራ ዓመታት ውጤታማ እንደነበሩ አስታውሰው በዚህም ቆይታቸው የሀገሪቱን ሕዝብና መንግሥት ማመስገን እንደሚፈልጉ ገልፀዋል፡፡

በተመስገን ሽፈራው