የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አዲስ የቡና የግብይት ስርዓት ተግባራዊ አደረገ

ሐምሌ 5፣2009

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ  የቡና ምርታማነትንና የወጪ ንግዱን ያሳድጋል የተባለ  አሰራርን  ከሀምሌ 1 ፣2009 ጀምሮ መተግበር  መጀመሩን  አስታወቀ ፡፡

የቡና ምርት ግብይት ስርዓቱን  ውጤታማ ለማድረግ  ባለፈው ሳምንት  የምርት ገበያ ማቋቋሚያ  አዋጅ ማሻሻያ  ተደርጎበት በህዝብ ተወካዮች  ምክር ቤት በመፅደቁ አዲስ አሰራር ተግባራዊ መደረጉን የምርት ገበያው አመልክቷል፡፡

የምርት ገበያው ዋና ስራ አስፈፃሚ  አቶ ኤርሚያስ  እሸቱ በአዲሱ የግብይት ስርዓት ለቡና ግብይቱ  የምርት ባለቤትነትንና  መገኛን  ገላጭ የሆነ የመኪና ላይ አዲስ የግብይት ስርዓት  መካተቱን ተናግረዋል፡፡አዲሱ አሰራር  ያለአገናኝ  አባል በቀጥታ መገበያየት ለሚፈልጉ  ግለሰቦች፣የህብረት ስራ ማህበራትና የንግድ ድርጅቶች አስፈላጊውን መመዘኛ  እስካሟሉ ድረስ  በቀጥታ መሳተፍ ያስችላቸዋል፡፡

በተጨማሪም በተሻሻለው  አዋጅ  የግብርና ምርቶች   የመጋዘን አገልግሎት  ድርጅት  ተመልሶ ከምርት ገበያው ጋር  እንዲዋሃድ  ተደርጓል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው  የደረቅ  ቡና  የደረጃ መጠንም ተዘርዝሮ  መቅረቡንም ገልፀዋል፡፡

ቡናን ዕሴት ጨምረው  ወደ ውጭ የሚልኩትንና  የሚነሳባቸውን የጥራት  ጥያቄ  ለመመለስ  ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ቡና ገዝተው እንንዲያቀነባብሩ መፈቀዱም ተገልጿል፡፡

አዲሱ የግብይት ስርዓት  አስፈላጊ የገበያ መርዘምን የሚያሳጥር  መሆኑንና  መተግበር ከጀመረ ወዲህም ለውጭ ገበያ በሚቀርበው ምርት  የመጠን  ለውጥ  መታየቱን ደግሞ  የቡናና ሻይ  ባለስልጣን  ም/ዳይሬክተር  ኢንጂነር ኤሌሮ አኒዮ ተናግረዋል፡፡

ቡና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 26  በመቶ ድርሻ  ሲኖረው  25 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝብ  ኑሮው  በቀጥታም  ይሁን  በተዘዋዋሪ ከቡና ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ  የቡና ምርትን  ለአለም  ገበያ የሚያቀርቡ  ከ400 በላይ ላኪዎች አሉ፡፡

ሪፖርተር ፡‑እፀገነት አሰፋ