ግዙፍ የበረዶ ግግር ከአንታርክቲክ መገንጠሉን ተመራማሪዎች ገለፁ

ሐምሌ 5፣2009

በምድራችን ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ የሚገኝ የአለማችን አንድ ግዙፍ የበረዶ ግግር ከአንታርክቲክ የበረዶ አካባቢ መገንጠሉን የዘርፉ ተመራማሪዎች አስታወቁ፡፡

6 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ይህ የበረዶ ግግር ዌልስ የተባለች የብሪታኒያ ግዛትን ሲሶ የሚያክል ስፋት አለው ነው የተባለው፡፡

‹‹ላርሰን ሲ›› ተብሎ በሚጠራ የበረዶ ክልል ላይ የተፈጠረው ይህ የተፈጥሯዊ ክስተት በአሜሪካ ሳተላይት መታየቱን ተነግሯል፡፡

በዚህም ሰፊ እርቀት ባለው የበረዶ ግግር መገንጠያ ላይ ውሃና ግልጽ የሆነ ክፍተት መታየቱን ተረጋግጧል፡፡

የበረዶ ግግሩ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከእናት አካሉ በፍጥነት የማይርቅ ባይሆንም በሂደት ግን በንፋስ እንቅስቃሴ አማካኝነት ወደ ሰሜናዊ የአንታርቲክ ክልል ሲጠጋ በቀጠናው በሚተላለፉ መርከቦች ላይ አደጋ ሊፈጥር እንደሚችል ተመራማሪዎች ከወዲሁ አስጠንቅቀዋል፡፡

የዘርፉ ተመራማሪዎች ክስተቱ እውን እንደሚሆን ከአስርት ዓመታት በላይ ሲጠብቁ እንደቆዩ ተነግሯል፡፡

ምንጭ፦ቢቢሲ