ኢትዮጵያ ከሁለት አመት በኋላ የራሷን ሳተላይት ልታመጥቅ ነው

ሐምሌ 5፣2009

ኢትዮጵያ ከሁለት አመት በኋላ ለምታመጥቀው ሳተላይት ግንባታ እየተካሄደ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ምክር ቤት የመጀመሪያ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡

በጉባኤው ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

የኤሮስፔስ ኢንስቲትዩት የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎችን ማፋጠን ቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን እንደሚገባ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ  የስፔስ ሳይንስ በኢትዮጵያ ከ40 ዓመታት በፊት ቢጀመርም ዓለም ከደረሰበት የስፔስ ቴክኖሎጂ አኳያ ወደኋላ የቀረ መሆኑንገልጸዋል።

በማሳያነትም ከ20 ዓመታት በፊት የጀመረችው ናይጄሪያ የራሷን ሳተላይት ከማምጠቅ አልፋ ለጎረቤት አገሮች ለማከራየት መብቃቷን አውስተዋል።

ዘርፉን ለማጎልበትም በ2005 ዓ.ም የተመሠረተው የእንጦጦ ስፔስ ሳይንስ ጥናትና ምርምር ማዕከል "የኢትዮጵያ ኤሮስፔስ ኢንስቲትዩት" በሚል በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስር እንዲዋቀር ተደርጓል።

የሬጉላተሪ፣ የምርምርና የልማት ዘርፍን አጣምሮ እንዲይዝ የተደረገው ኢንስቲትዩቱ፤ የ12 ዓመት የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ እቅድ መዘጋጀቱን ነው ሚንስትሩ የጠቆሙት።

የስፔስ ሳይንስ ዘርፈ ብዙ በመሆኑም ኢንስቲትዩቱን የሚመራ ከተለያዩ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የተወከሉ አባላትን ያቀፈ ምክር ቤት ተቋቁሟል።

ዘርፉ ካለው ፖለቲካዊ ፋይዳ አኳያም ምክር ቤቱ የአገር መከላከያ ሚኒስቴርን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን ጨምሮ ሌሎች ቁልፍ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎች እንዲካተቱ መደረጉ ተገልጿል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ 8ኛው ብሔራዊ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ተካሂዷል፡፡

ጉባኤውን በሰብሳቢነት የመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ችግር ፈቺ ምርምር ለሚያደርጉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መንግስት አስፈላጊውን በጀት እንደሚመድብ ገልፀዋል፡፡

ምንጭ:-ኢቢሲ እና ኢዜአ