የቀድሞው የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳሲልቫ የ9 ዓመት ተኩል እስራት ተፈረደባቸው

ሐምሌ 06፣2009

የቀድሞው የብራዚሉ ፕሬዝዳንት  ሉላ  ዳሲልቫ በተጠረጠሩበት የሙስና ክስ የ9 ዓመት ተኩል እስራት ተፈረደባቸው፡፡

ሉላ ዳሲልቫ የአገሪቱ ግዙፍ የነዳጅ ኩባንያ የሆነው ፔትሮ ብራስን በቢሊዮን ዶላሮች  በሙስና ሲመዘበር እጃቸው አለበት በሚል ነው እስራቱ የተበየነባቸው፡፡

የአገሪቱ ፌደራል ፍርድ ቤት ኩባንያው  የአገሪቱ የቀድሞው ፕሬዝዳንት የ1.2 ቢሊዮን ዶላር ጉቦ በመቀበል ጥፋተኛ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ በሚል የፍርድ ውሳኔውን እንዳሳለፈ አስታውቋል፡፡

የእስር ፍርድ ውሳኔው ይተላለፍ እንጅ ሉላ ዳሲልቫ  ይግባኛቸውን እስከሚያሰሙ ድረስ ተፈፃሚ እንደማይሆን ተመልክቷል፡፡

ይሁን እንጂ ተከሳሹ የቀድሞው ፕሬዝዳንት የተላለፈባቸው ውሳኔ ፖለቲካው ሴራ ያዘለ ነው በሚል ተቃውመውታል፡፡

እ.ኤ.አ ከ2003 እስከ  2011 ድረስ  የብራዚል ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት  ሉላ ዳሲልቫ፣ በቀጣዩ ዓመትም ዕጩ ፕሬዝዳንት ሆነው ይቀርባሉ ተብሎ ሲጠበቅ የአሁኑ የፍርድ ውሳኔ  መተላለፉ በብራዚላዊያን ዘንድ  የተለያዩ ሀሳቦችን ያጫረ ሆኗል፡፡

ምንጭ ፡‑ ሽንዋ