ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለሚያካሄዱ የትምህርት ተቋማት መንግስት ድጋፍ ያደርጋል - ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ

ሐምሌ 6፤2009

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ችግር ፈቺ ምርምር ለሚያደርጉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መንግስት አስፈላጊውን በጀት እንደሚመደብ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ፡፡

ባለፈው አመት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 22 ቢሊዮን ብር በጀት የተመደበ ቢሆንም ለችግር ፈቺ ምርምሮች ትኩረት እንዳልተሰጠ ነው ያብራሩት፡፡

የብሔራዊ ሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ምክር ቤት 8ኛ መደበኛ ጉባዔውን ባካሄደበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲዎችና በኢንደስትሪው መካከል ያለውን ትብብር ማሳደግ ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡

ይህንኑ ተፈጻሚ ለማድረግም ወደፊት እንዳስፈላጊነቱ አስገዳጅ ህግ ሊወጣለት እንደሚችል የተናገሩት፡፡

 የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በ226 ተመራማሪዎች ለቀረቡ የምርምር ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ አመትም 56 የምርምር ፕሮጀክቶች የ179 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ነው ያብራሩት፡፡

የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ ፍላጎት ለማሟላትም ለአስር አመታት የሚቆይ በ20 ዘርፎች የቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ነው የገለጹት፡፡