ዩኔስኮ ለዓለማችን ቅርሶች የበለጠ ጥበቃ እንዲደረግ ጥሪ አቀረበ

ሐምሌ 06፤2009

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ ለዓለማችን ቅርሶች የበለጠ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቀረበ፡፡

የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ በደቡባዊ ፖላንድ በምትገኘው ክራኮው ከተማ ለ10 ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን 41ኛ አጠቃላይ ጉባኤ 235 ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ተጠናቅቋል፡፡

ኮሚቴው በመጥፋት የአደጋ ስጋት ካለባቸው የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ጨምሮ 3 ቅርሶችን ከመዝገቡ ማስወጣቱንም አስታውቋል፡፡

በጉባኤው 21 አዳዲስ ስፍራዎች በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ሲሆን ይህም በዓለማችን የተመዘገቡ ቅርሶችን ቁጥር ወደ 1 ሺህ 73 ከፍ አድርጎታል፡፡

አዲስ የተመዘገቡት 21 ቅርሶች ከኤርትራ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከቻይና፣ ከአርጀንቲና፣ ህንድ፣ ጃፓን፣ ኢራን፣ ሩሲያ፣ ጀርመን፣ ፖላንድ፣ ጣልያን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ብራዚል፣ ግሪንላንድ፣ ዳውሪያ እና ሄብሮን የተውጣጡ ሲሆን 18ቱ ባህላዊ፣ ቀሪዎቹ 3 ቅርሶች ደግሞ ተፈጥሮአዊ ናቸው፡፡

ቻይና በዩኔስኮ 52 ቅርሶን ስታስመዘግብ ዘንድሮ አንጎላና ኤርትራ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅርሶቻቸውን በመዝገቡ ላይ ማስፈር የቻሉ አገራት ናቸው፡፡

በጉባኤው ላይ ከ126 አገራት የተውጣጡ ከ2 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ታድመዋል፡፡