የፍርድ ቤቶችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የመፍትሄ አቅጣጫዎች መቀመጣቸው ተገለጸ

 ሐምሌ 5፣2009

በፍርድ ቤቶች አካባቢ የሚታዩትን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ፤ የህብረተሰቡን ቅሬታ ለማስቀረት የመፍትሄ አቅጣጫዎች መቀመጣቸው ተገልጿል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዝዳንትና የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ሰብሳቢ አቶ ዳኜ መላኩ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ በፍርድ ቤቶች በአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ምክንያት ተገልጋዮች ቅሬታ ማንሳታቸውን ገልጸዋል፡፡

በ2010 መፍትሄ እንዲያገኙ እቅድ ከተያዘባቸው ጉዳዮች ውስጥ ከጉዳዩ ፍሰት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የዳኞች ቁጥርን ማሟላት አንዱ ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓትም የእጩ ዳኞችን ምልመላ እየተካሄደ ሲሆን አስፈላጊውን መስፈርት ያሟሉ ዳኞች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው እንደሚጸድቅ ነው የተናገሩት፡፡  

የጉዳዮች መጓተትና የቀጠሮ መራዝምን ለማስወገድ ሲባልም የግልጽነትና ተጠያቂነትን ስርዓቱን የሚያጎለብቱ ጥብቅ የክትትልና የቁጥጥር አሰራር ሂደቶችን እንደሚከተሉ ነው አቶ ዳኜ መላኩ ያብራሩት፡፡

ለአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ማነስ ሌላው ምክንያት በቂና ምቹ የማስቻያ ቦታ አለመኖርና የቢሮ ጥበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህ እንደ መፍትሄ አቅጣጫ የተቀመጠው ደግሞ በአጭር ጊዜ እቅዱ የተገጣጣሚ ቤቶች ግንባታ እየተካሄደ ሲሆን ለዘለቄታዊ መፍትሄው ደግሞ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዘመናዊ ህንፃ ለማስገንባት ዲዛይኑ ተጠናቆ የቦታ ጥያቄ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

  በስራ ላይ ያለውን የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያውን በጥናት በመፈተሽና ያሉትን ክፍተቶች በመሙላት እንዲሁም ደረጃ ያልወጣላቸውን ድንጋጌዎች ደረጀ በመስጠት የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያን በማሻሻል የፍርድ ውሳኔውን ተገማችነትና ወጥነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ነው ያብራሩት፡፡

እንድ አቶ ዳኜ መላኩ ማብራሪያ ከሆነ የተገልጋዮች ሃሳብ መግለጫ ሁኔታዎችን፤ በዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን ለማጠናከር፤ የመዛግብት አያያዝና እንክብካቤን ለማሻሻል፤ በሬጅስትራር አካባቢ የሚታዩትን አየሰራር ችግሮችን ለመፍታት የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተቀምጠውላቸዋል፡፡

በዲባባ ቡራዩ