ከሳውዲ ተመላሽ ዜጎች ወደ ስራ እንዲገቡ ማህበራት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

ሐምሌ 7፣2009

ከሳውዲ ተመላሽ ዜጎች በፍጥነት ወደ ስራ መግባት እንዲችሉ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አሳሰቡ።

አባላቱ በበኩላቸው ከሳውዲ ተመላሽ ዜጎች እንዲቋቋሙ፣ የስራና የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የማመቻቸቱን ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላት ከሳምንታት በፊት ባደረጉት ስብሰባ ከሳውዲ አረቢያ የሚመለሱ ዜጎች ወደ አገራቸው ከገቡ በሃላ የስራ ዕድል እንዲያገኙ፣  እንዲቋቋሙና መማር የሚፈልጉ ዜጎችም የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ለማድረግ በተለያዩ  የንግድ ዘርፍ የተሰማሩ አከላትን በማነጋገር ሁኔታዎችን ለዜጎች ለማወያየት ውሳኔ  አሳልፈው ነበር።

ውሳኔው ከምክር ቤቱ የበላይ ጠባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር እንደተወያዩበት ገልጸዋል።

የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላቱን እቅድ የተቀበሉት ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ንብረታቸውን ይዘው የሚመለሱ ዜጎች በፍጥነት ወደ ስራ መግባት እንዲችሉ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ምንም ንብረት ሳይዙ የሚመለሱ ዜጎች ደግሞ በቂ ስልጠና እንዲያገኙ  በማድረግ በአገሪቱ  ባሉ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች የስራ ዕድል እንዲያገኙ ምክር ቤቱ እንዲሰራ አሳስበዋል።

ፕሬዝዳንቱ ዜጎቹ በቂ ማቋቋሚያ እንዲያገኙ አባላቱ ሊሰሩ  ያቀዱትን የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

አባላቱ በበኩላቸው ከሳውዲ ተመላሽ ዜጎች እንዲቋቋሙ፣ የስራና የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የማመቻቸቱን ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ወደ ፊት ለሚከሰቱ ተመሳሳይ ችግሮች ቀድመው ለመዘጋጀት እንዲህ አይነቱን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉበትም ገልጸዋል።

ሪፖርተር:-ሜሮን በረዳ