በህዋ አዲስ ደማቅ ‹‹ጋላክሲ›› ማግኘታቸውን ተመራማሪዎች ገለፁ

ሐምሌ 10፣2009

የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች በዮኒቨርስ በእጅጉ ደማቃማ አዲስ ‹‹ጋላክሲ›› ማግኘታቸውን አስታወቁ፡፡

‹‹ጋላክሲ›› በህዋ ውስጥ በስበት ሀይል የተያያዙ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩ የኮከቦች፣ የጋዝ፣ የአቧራና የሌሎች ንጥረ ነገሮች ስብስብ ስርዓት ነው፡፡

በዩኒቨርስ ውስጥ በመቶ ቢሊዮን የሚቆጠሩ ጋላክሲዎች ሲኖሩ አሁን የምንኖርባት ፕላኔት ደግሞ ‹‹ሚልኪዌ›› በሚባል ጋላክሲ ላይ ውስጥ ይገኛል፡፡  

አሁን ላይ ደግሞ የዘርፉ ተመራማሪዎች ከወትሮ የተለየ በእጅጉ ደማቅ የሚባል ‹‹ጋላክሲ›› ስፔን በሚገኘው በግራን ቴሌስኮፒዮ ካናሪያስ በተባለ ቴሌስኮፕ አማካኝነት ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

በትንሹ በ10 ሺህ ሚሊዮን የብርሃን ዓመት እርቀት የሚገኘው አዲሱ ጋላክሲም ከሚልኪዌ በአንድ ሺህ እጥፍ ደማቃማ እንደሆነ ተመራማሪዎቹ አመልክተዋል፡፡

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የክዋክብት ስብስብ የሆነው ጋላክሲ ከሌሎች አቻዎቹ ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩና ከፍተኛ ሀይል ያላቸው ኮከቦች ስለሚገኙበት ነው ተብሏል፡፡

አዲሱ ጋላክሲ የተገኘውም ተመራማሪዎች በአሜሪካ የህዋ ምርምር አስተዳደር/ናሳ/ ሳተላይትና ከአውሮፓ የህዋ ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት ህዋን  ከቃኙ በኃላ እንደሆነ ታውቋል፡፡

በቀጣይም በጋላክሲው ውስጥ ያሉት ኮከቦች አፈጣጠርና የሚይዙት ንጥረ ነገር ዙሪያ ምርምር እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡

ምንጭ፦ሽንዋ