የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን ለአርብቶ አደሩ በማድረስ ምርታማነትን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገለፀ

ሐምሌ 10፣ 2009

የተሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን ለአርብቶ  አደሩ በማድረስ ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የእንስሳትና አሳ ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የእንስሳት ሀብት ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ  አኳያ ምርጥ ዘርን ለሁሉም አርብቶ አደር ለማዳረስ ባይቻልም  በሰው ሰራሽ ዘዴ   እንስሳትን በማዳቀል ለአርብቶ አደሩ ለማዳረስ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አብርሃም ተስፋዬ ለኢቢሲ ገልፀዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የእንስሳትን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፣ የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል  እና የአገሪቱን  ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ የእንስሳት ሀብት ልማት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በእንስሳቱ ሀብት ልማቱ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችለው ዘንድ በቅድሚያ የእንስሳት ማሻሻያ ዝሪያ ማሻሻያ ፖሊሲ በመንደፍ ረቂቁም ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት እየተመከረበት እንደሆነም  አቶ አብረሃም ተናግረዋል፡፡

የእንስሳት ሀብት ልማት ፍኖተ ካርታው ሲዘጋጅም በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ እንደሆነ የተናገሩት አቶ አብረሃም፣ በተለይም የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ስራዎች በስፋት አለመሰራት፣የመኖ እጥረት እና የእንስሳት ጤና አጠባበቅ በሚፈለገው አግባብ ተጠብቆ ያለመሄድ ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

በእንስሳት ዝርያ ማሻሻያው ዘርፍ የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍም  ብሄራዊ የሰው ሰራሽ እንስሳት ማዳቀያ ዘዴ ማእከል የምርጥ ዘር አባላዘር በማምረት ለአርብቶ አደር ክልሎች እንዲሰራጭ መደረጉን አቶ አብርሃም ተናግረዋል፡፡

ከአምና ጀምሮ እንስሳት በሚበዙባቸው ቆላማ የአርብቶ አደር አካባቢዎች የመኖ ማልማት ስራ በሰፊው እየተከናወነ  መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ምርታማነትን ሊያጓድሉ የሚችሉ በሽታዎችን  በመለየት ክትባቶች በወቅቱ የመስጠት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴር በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅድ  አገር በቀል እንስሳትን ከውጭ ምርጥ ዘሮች ጋር በማዳቀል  የወተት ምርታማነትን በ10 እጥፍ ማሳዳግ ያለመውን  እቅድ ለማሳካት ትኩረት ሰጥቶ  እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር ፡‑ ድርቤ መገርሳ