የአሜሪካዋ ሆኑሉሉ እግረኞች ሞባይላቸውን እያዩ የመኪና መንገድ እንዳይሻገሩ ልትከለክል ነው

ሐምሌ 24፣2009

የአሜሪካዋ ሆኑሉሉ ከተማ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል እግረኞች ሞባይላቸውንና ሌሎች ዲጂታል መሳሪያዎችን እያዮ የመኪና መንገድ እንዳይሻገሩ የሚከለክል ህግ አወጣች፡፡

ከሁለት ወራት በኋላ   ጥቅምት ላይ የሀዋይ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ሆኑሉሉ ከተማ ተግባራዊ የሚሆነው ይህ ህግ እግረኞች ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሞባይልን ጨምሮ ዲጂታል መሳሪያዎች ሲጠቀሙ በትራፊክ አደጋ ሊደርስ የሚችለውን የሞት አልያም ሌሎች ጉዳቶችን ለመቀነስ ነው፡፡

አዲሱን ህግን ተላልፈው የተገኙ ሰዎች በመጀመሪያ ቅጣት ከ15 እከ 35 ዶላር የሚከፍሉ ሲሆን ተደጋጋሚ ጥፋት ሲያጠፉ ደግሞ እስከ 99 ዶላር ክፍያ እንዲከፍሉ እንደሚገደዱ በድንጋጌው ተመልክቷል፡፡

ይሁንና እግረኞች በአደጋ ጊዜ እርዳታ ሲሹ የመኪና መንገድ እየተሻገሩ የዲጂታል መሳሪያዎቹን መጠቀም እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

መንግስት በአዲሱ ህግ ግለሰቦች መብት ላይ ጣልቃ በመግባት እጁን አስረዝሟል በማለት ጥቂት ሰዎች ህጉን ነቅፈውታልም ነው የሚባለው፡፡

ምንጭ፦ሽንዋ