ናይጀሪያ ከተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጋር በመሆን የኢንዱስትሪ ማዕከላትን ልትገነባ ነው

ሐምሌ 26፣2009

ናይጀሪያ ከተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጋር በመሆን የኢንዱስትሪ ማዕከላትን ልትገነባ ነው፡፡

በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ  ልማት ድርጅት   የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ አባል አገራት (ኢኮዋስ) ተወካይ  ጄን ባኮሌ ናይጀሪያ በአቡጃ ሰፋፊ የኢንዱስትሪ ዞንና ፓረኮችን ግንባት ለማካሄድ  ድርጅታቸው ድጋፉን እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት  ናይጀሪያ ከሶስት ወራት በፊት ይፋ ያደረገችውን የኢኮኖሚ ማገገሚያና የእድገት እቅድ ለማሳካት የሚገነቡት የኢንዱስትሪ ማዕከላት መሰረተ ልማቶች ግንባታ ወሳኝነት አላቸው፡፡ይህም የናጄሪያን የኢንዱስትሪ አብዮት እቅድ ለማሳካት የተዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በሁለቱ ወገኖች ትብብር የተነደፉት የኢንዱስትሪ ማዕከላት ልማት  የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችንና የህዝብና የግሉ ዘርፍ አጋርነትን የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ፡፡

ለዚህም ይረዳ ዘንድ በዩኒዶና በናይጄሪያ  አማካኝነት ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ያስመዘገበችውን ስኬት ቦታው ድረስ  በመሄድ ልምድ መቀሰሙ ተመልክቷል፡፡

ዩኒዶም በተሞክሮው ጥናት የኢትዮጵያ ልምድ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ትብብርና ውህደት አይነተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው አመልክቷል፡፡

የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅቱ የኢትዮጵያን የዘርፉ ተሞከሮ በመቀመር የናይጀሪያን ኢንዱስተሪ ማበልፅግ የሚያስችሉ የኢንዱስትሪ ማዕከላትን ለመገንባት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን አመልክቷል፡፡

ምንጭ ፡‑ ዘ ጋርዲያን ናይጀሪያ