አዲሱ የአሜሪካ ማዕቀብ በአገሯ ላይ የታወጀ የንግድ ጦርነት መሆኑን ሩስያ አስታወቀች

ሐምሌ 27፣2009

አሜሪካ በሩሲያ ላይ የጣለችው አማዕቀብ በይፋ የንግድ ጦርነት ማወጁዋን እንደሚያመለክት የሩሲያው ጠቅላይ ሚንስትር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ተናገሩ፡፡

በቅርቡ በአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ፀድቆ በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትላንት የተፈረመውን ማዕቀብ ጠቅላይ ሚንስትሩ ክፉኛ ኮንነውታል ተብሏል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት ከሆነ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ጄ ትራምፕ ስልጣናቸውን በመጠቀም ረገድ ደካማ መሆናቸው ያሳያል።

ማዕቀቡ ሀገራቸው ከአዲሱ የአሜሪካ መንግስት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል የጀመረችውን ጥረት የሚያጨልም መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ተአምር ካልተፈጠረ በስተቀር የማዕቀቡ ህግ ለቀጣዮቹ አስርት ዓመታት ፀንቶ እንደሚቆይ ተናግረዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ፡፡

በሀገራቸው ላይ የተወሰነው አዲሱ ማዕቀብ በቀጣይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ከስልጣን ለማንሳት በር የሚከፍት እንደሆነም አስጠንቅቀዋል፡፡

ማዕቀቡ ሩሲያ በ2016 የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ምርጫ ‹‹ጣልቃ ገብታለች›› እንዲሁም በዮክሬን ባላት ሚና መቀጣጫ ለማድረግ ታልሞ የተዘጋጀ ህግ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ 

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ጄ ትራምፕ ህጉን ሲያፀድቁ ማዕቀቡ ሰፊ ጉድለቶች እንዳሉት በመናገር የምክር ቤቱ አባላት በማዕቀቡ አወሳሰን ላይ ስልጣናቸውን አስረዝመዋል በማለት ነቅፈዋቸዋል፡፡

የማዕቀቡ ህግ አሜሪካውያን በሩሲያ የሀይል ፕሮጀክት የሚያፈሱትን መዋእለንዋይ መጠን ይገድባል፤ የሀገሪቱ ኩባንያዎችም ከሩሲያ ጋር የንግድ ግንኙነት ለማከናወን ይበልጥ አዳጋች ያደርግባቸዋል ነው የሚባለው፡፡

ጀርመን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ አገራት ማዕቀቡ የአለም አቀፍ ህግን የሚጥስ መሆኑን በመጥቀስ በሩሲያ የሚንቀሳቀሱ የአውሮፓ ኩባንያዎችን ይጎዳል በማለት ሁኔታው እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

በ2016 የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ምርጫ ዶናልድ ትራምፕን ደግፋ በምርጫው ጣልቃ ገብታለች ብለው የአሜሪካ ሹማምንት የሚሰንዝሩባትን ውንጀላ የምትቃወመው ሩሲያ ለማዕቀቡ አፀፋዊ ምላሽ መስጠቷ የሚታወስ ነው፡፡ 455 በሀገሯ የሚገኙ አሜሪካ ዲፕሎማቶችን ቀንሳለች።

 አውሮፓውያን በማዕቀቡ ቅሬታቸውን ካሰሙ በሃላም አሁን ላይ ህጉ ለዝቦ አልያም ተለሳልሶ ተግባራዊ እንዲሆን በመወሰኑ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ጄን ክላውድ ጀንከር መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ባላንጣ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሁለቱ ሀገሮች በአዲሱ ማዕቀብ ወትሮም ቢሆን ሻክሮ የቆየው ግንኙነታቸው ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚያደርገው ተገምቷል፡፡  

ምንጭ፦ቢቢሲ