ኢትዮጵያ ተሽከርካሪዎችን ለመስራት አቅዳለች

ሐምሌ 29፣2009

ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት ውስጥ በአገር ውስጥ ተሽከርካሪዎችን ለማምረት ማቀዷ ተገለጸ።

በ2025 ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ በመሸጋገር መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ የመሰለፍ እቅድን የያዘችው ኢትዮጵያ እቅዷን ለማሳካት የጨርቃጨርቅና  አልባሳትን ጨምሮ ሰፊ ሰራተኞችን ለሚይዙ የአምራች ዘርፎች ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።

በሌላ በኩል እንደ መስፍን ኢንጂነሪንግ፣ በላይአብ ሞተርስ፣ ሊፋን ሞተርስ፣ ሂንዱና  ቢሾፍቱ ኦቶሞቲቭን የመሳሰሉ  የመኪና መገጣጠሚያዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ስራ ላይ ናቸው።

የመኪና መገጣጠሚያዎቹ  የተለያዩ መለያ ስያሜዎች ያሏቸው ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን በማምረት ለአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች ከዚህ ስራቸው ባለፈ የተለያዩ መኪናዎችን በኢትዮጵያ ውስጥ የማምረት እቅድ አላቸው፡፡

በላይ አብሞተርስ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2020 ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ ለማምረት ካቀዱት ድርጅቶች አንዱ ነው።

በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2014 ፋብሪካውን በአዲስ አበባ የከፈተው የቻይናው ሊፋን ግሩፕ በቀን 20 ተሽከርካሪዎችን ይገጣጥማል። 

ፋብሪካው በረዥም ጊዜ እቅዱ  በኢትዮጵያ ሞትር ሳይክሎችን ጨምሮ ተሽከርካሪዎችን  እንደሚያመርት አስቀምጧል፡፡

የኢትዮጵያ ብረታ ብረት ልማት ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት ሌሎች የመኪና አምራች ኢንዱስትሪዎችም በቅርብ አመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ተሽከርካሪዎች ያመርታሉ ብሏል፡፡