ጃኮብ ዙማ በስልጣናቸው እንደሚቆዩ አረጋገጡ

ነሃሴ 02፤ 2009

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ የፓርላማውን አብላጫውን ድምጽ በማግኘታቸው በስልጣናቸው እንደሚቆዩ አረጋግጠዋል፡፡

ዙማ ከፓርላማው አባላት የ198ቱን ድጋፍ ሲያገኙ 177ቱ ደግሞ ከስልጣናቸው ይውረዱ በማለት ድምጽ ሰተው ነበር፡፡

ይህ ማለት 40 የገዢው አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ አባላት ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማን በመቃወም ድምጽ እንደሰጡ ነው ቢቢሲ የዘገበው፡፡

የደቡብ አፍሪካ ፓርላማ በፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ላይ በሚስጢር የመተማመኛ ድምጽ እንዲሰጥ አፈ ጉባኤው መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ፓርላማው ይህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጉዳዩን ለህገ መንግስተዊ ፍርድ ቤት ከወሰዱት በኋላ ነበር፡፡

ፕሬዝዳንቱ በቂ የመተማመኛ ድምጽ ባያገኙ ኖሮ ሀገሪቱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ አዲስ ፕሬዝዳንት ሊኖራት ይችል ነበር፡፡

በፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ መንግስት ውስጥ የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እየፈጠረ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡

ይሁንና ጃኮብ ዙማ ይህን ሁሉ ጫና አልፈው ፓርላማው በስልጣናቸው እንዲቆዩ በአብላጫ ድምጽ ወስኖላቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በዚህኛው የመተማመኛ ድምጽ አሰጣጥ ላይ ያገኙት ድምጽ ከቀደሙት አነስተኛ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

ምንጭ፡ ቢቢሲ