የናይጄሪያ የቀድሞ የነዳጅ ሚንስትሯ ቅንጡ መኖሪያ ቤት በሙስና ምክንያት ተወረሰ

ነሀሴ3 ፣2009

የናይጄሪያ መንግስት በሙስና ቅሌት ፍርድ ቤት ያቆማቸውን የቀድሞ የነዳጅ ሚንስትሯን ከ37 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ቅንጡ መኖሪያ ቤት በሙስና ምክንያት ወረሰ፡፡

የቀድሞዋ የነዳጅ ሚንስትር ዲዛኒ አሊሶን ማዱኬ በሌጎስ በፍርድ ቤት ትእዛዝ የተወረሰባቸው ቤት በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ሌጎስ አቅራቢያ ባናና በተሰኘ ደሴት ላይ ባለ እጅግ ውድ መንደር የገዙት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ ቀርበው በክሱ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ እና እንዲከላከሉ በተሰጠው 14 ቀናት ውስጥ ባለመቅረባቸው ቤቱን እንደተወረሰ አስታውቋል፡፡ የቀድሞ የናይጀሪያ የነዳጅ ሚንስትር  ቤቱን በማከራየት ያገኙትን 3 ሚሊዮን ዶላርም ለመንግስት ገቢ እንዲደረጉ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

የ56 ዓመቷ የቀድሞ ሚንስትር  በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች በሚቆጠር አለም አቀፍ የሙስና ቅሌት ተጠርጥረው በፍርድ ቤቱ ምርምራ ስር ቆይተዋል፡፡

በፍርድ ቤቱ አሁን የተወሰደው እርምጃ በሙስና የተመዘበሩ የመንስግስት ሀብትን የማስመለስ እቅድ አንዱ አካል ሲሆን ከናይጄሪያ የደዳጅ ድርጅት ብቻ 153.3 ሚሊዮን ዶላይ የሚገመት ገንዘብ እንደተጭበረበረ ተገልጿል፡፡

ምንጭ፡‑ ሲጂቲኤን