የኬንያ ምርጫ ነፃና ፍትሀዊ ነው፦ የምርጫ ታዛቢዎች

ነሀሴ 4 ፤2009

ዘንድሮ የተካሄደው የኬንያ አጠቃላይ ምርጫ ነፃና ፍትሀዊ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ፤ የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎች አስታወቁ፡፡

በቅድመ ምርጫ ውጤቱ የወቅቱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንዳሸነፉ ቢነገርም ተፎካካሪያቸው ራይላ ኦዲንጋ ግን የኮሚሽኑ ኮምፒውተር በመረጃ ቀበኞች በመጠለፉ ምክንያት የምርጫው ውጤት ተጭበርብሯል ነው ያሉት፡፡

በአሁን ወቅትም የቅድመ ምርጫ ውጤቱን ያልተቀበሉ ኬንያውያን በአደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን እያሰሙ እንደሚገኙ ነው የሚነገረው፡፡

በዚህም ተቃውሞ የተፈጠረውን ሁከትና ብጥብጥ ለመቆጣጠርም የሀገሪቱ ፀጥታ አካላት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

በዛሬው ዕለት የወጣው የምርጫው ጊዜያዊ ውጤት እንደሚያሳየው ድምጽ ከሰጡት ኬንያዊያን ውስጥ ፕሬዝዳንት አሁሩ ኬንያታ 54 በመቶው ገደማ ሲያገኙ ተቀናቃኛቸው ራይላ ኦድንጋ ደግሞ የ45 በመቶ የሚጠጋውን መራጭ ህዝብ ይሁንታ አግኝተዋል ተብሏል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የኬንያን ምርጫ ኮሚሽንን ስራ በማወደስ ምርጫው የተሳካ እንደነበር አመልክቷል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ታዛቡ ባለሞያዎች በበኩላቸው በምርጫው ሂደት ምንም አይነት የተደራጀ የማጭበርበር ተግባር አለማየቱንና ተቃዋሚው ወገን ውጤቱን በጸጋ እንዲቀበል አሳስቧል፡፡

የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን የምርጫው ይፋዊ ውጤት እስኪገለፅ ድረስ ህዝቡ በትዕግስት እንዲጠብቅ ማሳሰቡን ያታወሳል፡፡

የምርጫውን ሂደት በዋናነት የምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ፣ አፍሪካ ህብረት፣ አውሮፓ ህብረት፣ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ  ታዝበውታል፡፡

ምንጭ፦ዘ ስታር፤ ቢቢሲ