የአጎዋ ውይይት ያለውጤት ተጠናቀቀ

ነሀሴ 6 ፤2009

የአፍሪካ ምርቶች በአሜሪካ ገበያ ከቀረጥ እና ኮታ ነጻ እድል /አጎዋን/ ለመከለስ በሁለቱ ወገኖች ልኡካን ወገኖች መካከል በቶጎ ሲደረግ የነበረው ውይይት ያለውጤት መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

በውይይቱ ላይ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራም ዋንኛ የንግድ ተደራዳሪ ሮበርት ላይትዘር እና ሌሎች ባለስልጣናት የተገኙበት ሲሆን ከንግድ ዘርፉ ስፋት አንጻር ተጠቃሚ የሚሆኑት ሀገራት እጅጉን አነስተኛ ነው ተብሏል፡፡

ይህ ሁኔታ በሚቀጥሉት አመታት ውስጥ ለውጥ የሚያመጣ ከሆነ የሚታሰብበት ሲሆን ጥሩ ውጤት ለማምጣት ግን ተጠቃሚ ሀገራት የንግድ ሁኔታቸውን ሊያጤኑት እንደሚገባ ተነግሯል፡፡

የቶጎ ንግድ ሚኒስቴር በርናደቴ ሌግዚም ባላውኪ በበኩላቸው ሁሉም ሀገራት ከስምምነቱ ተጠቃሚ ሊሆኑ ያልቻሉበትን ምክንያቶች እየለየን ነው ብለዋል፡፡

በፈረንጆቹ 2008 በአሜሪካ እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል የነበረው የንግድ ገቢ ልዩነት 64 ቢሊዮን የነበረ ሲሆን በአሁን ሰዓት ግን ወደ 7 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር አሽቆልቁሏል፡፡

በአጎዋ የንግድ ስምምነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተወሰኑት 38 ሀገራት በሚፈለገው ደረጃ በእድሉ ተጠቃሚ እንዳልሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

የአጎዋ ስምምነት በባራክ ኦባማ አስተዳደር ዘመን የተፈጸመ ሲሆን በፈረንጆቹ እስከ 2025 ድረስ ብቻ ተፈጻሚ የሚሆን ነው ተብሏል፡፡

ምንጭ፡ ሮይተርስ