ኬንያ ከምስራቅ አፍሪካ እናቶች አነስተኛ የልጆች ቁጥር የተመዘገበባት አገር ሆነች

ነሀሴ 23 ፤2009

ኬንያ ከምስራቅ አፍሪካ እናቶች አነስተኛ የልጆች ቁጥር የተመዘገበባት አገር ሆነች፡፡

የኬንያ እናቶች አማካይ የውልደት ምጣኔ 3.9 በመሆኑ ከጎረቤት የምስራቅ አፍሪካ አገራት አንፃር ዝቅተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የተባበሩ መንግስታት ድርጅት አለም አቀፍ የህዝብ ቁጥር መረጃን መሰረት በማድረግ በወጣው ሪፖርት ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ብሩንዲ አንድ እናት በአማካይ 6 ህፃናት በመውለድ  ቀዳሚ ሆናለች፡፡ የኡጋንዳ 5.4፣ ኢትዮጵያ 4.6 እና  ሩዋንዳ 4.2 አማካይ የውልደት መጣኔ የተመዘገበባቸው አገራት በመሆን በቅደም ተከተል ያውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ አነስተኛ የውልደት መጠኔ ካላቸው ኬንያና ሩዋንዳ በመከተል በሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን የተመድ  አለም አቀፍ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

ኬንያ በ3.9 የውልደት መጠኔ ከምስራቅ አፍሪካ አነስተኛ ቁጥር የተመዘገበባት ብትሆንም፣ ከአለም አማካይ 2.5 የወልደት ምጣኔ አንፃር ሲታይ ግን ከፍተኛ መሆኑ አመላካች ነው ብሏል ሪፖርቱ፡፡  አፍሪካ በአህጉር ደረጃ ያላት የውልደት ምጣኔ ደግሞ  4.6 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

እ.ኤ.አ 1978 በኬኒያ አንድ እናት በአማካኝ 8 ልጆች ትወልድ የነበረ ሲሆን ባለፉት 40 አመታት ውስጥ የህዝቡ ንቃተ ህሊና እያደገ በመምጣቱ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት መስፋፋት አሁን ያለውን ውጤት እንዳስገኘ ተገልጿል፡፡

በኬንያ የቤተሰብ ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም አጠቃላይ የህዝብ ቁጥሩ አሁን ካለበት 49 ሚሊዮን እስከ 2050 በእጥፍ በመጨመር 96 ሚሊዮን ይደርሳል የሚል ግምት ተሰጥቶታል፡፡

ኬንያ አሁን ካስመዘገበችው አነስተኛ የውልደት ምጣኔ አንፃር ሲታይ ወደፊት ምርታማ የሆነው የወጣቱ ቁጥር ቀንሶ በእድገቷ ላይ ጋሬጣ እንዳይሆንባት ግን ተሰግቷል፡፡

ምንጭ፡‑ ሲጂቲኤን