የቻይና - አፍሪካ ሳይንሳዊ ትብብር ወደ አዲስ ምእራፍ እየተሸጋገረ መሆኑ ተነገረ

ነሃሴ 30፤2009

ቻይና በሳይንስ፣በቴክኖሎጂ እና በፈጠራው ዘርፍ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላት አጋርነት አህጉሪቱ ያጋጠማትን  ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ምህዳራዊ ችግሮች ለመቅረፍ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ፡፡

በቻይና የሳይንስ አካዳሚ የዓለም አቀፍ ትብብር ቢሮ ዳይሬክተር ጀኔራል ካኦ ጂንገኡ  ቻይና በትምህርት፤ በሳይንስ፤ በቴክኖሎጂ እና በባህል ዘርፍ ከአፍሪካ ሀገሮች ጋር ያላት ግንኙነት ቁልፍ ተግባሮች ናቸው ብለዋል፡፡  

ዳይሬክተር ጀኔራሉ ካኦ ቻይና የአፍሪካ ወጣት ተመራማሪዎች የሀገራቸውን ልማት እንዲያሳድጉ በአከባቢ፣በግብርና ፣በጤና እና በውሃ አያያዝ ላይ በስልጠና እንደምትረዳ ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተር ጀኔራሉ ይህንን የተናገሩት በናይሮቢ በተካሄደው የአየር ንብረት፤ ሥነ ምህዳር እና  መተዳደሪያዎች ኮንፈረንስ ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የአፍሪካና የቻይና ተመራማሪዎች በተካፈሉበት በዚህ ኮንፍረንስ ላይ  የአፍሪካ እና የቻይና ሳይንቲስቶች በአህጉሪቱ የአረንጓዴ ልማትን እና ዘላቂ ልማትን ለማምጣት የሚያስችሉ አዳዲስ ስልቶች ላይ ተወያይተዋል፡፡  

ምንጭ- ሽንዋ