በማህፀን ውስጥ ፅንስ መፍጠር የማይችሉ ጥንዶችን የልጅ ባለቤት የሚያደርግ የህክምና ማዕከል በምስራቅ አፍሪካ ሊከፈት ነው

መስከረም 02፣2010

በማህፀን ውስጥ የመፀነስ ችግር ለሚገጥማቸው ጥንዶች   ከማህፀን ውጭ በሚደረግ ፅንሰት  እንዲወልዱ የሚያስችል የህዝብ ሆስፒታል በምስራቅ አፍሪካዋ  ኡጋንዳ በሚቀጥለው አመት ሊከፈት ነው።

በማህፀን ውስጥ የመፀነስ ችግር ሲገጥም ከማህፀን ውጭ የወንዱን የዘሬ ፍሬና የሴቷን እንቁላል በመውሰድ ቤተ ሙከራ ውስጥ እንዲዋሃዱ በማድረግና ፅንሱን ወደ ማህፀን በማስገባት በሚፈጠር እርግዝና(IVF) ሆስፒታሉ በምስራቅ አፍሪካ ያሉ  ሴቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።

ከሜርክ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በአሁኑ ጊዜ በዩጋንዳ ካምፓላ እየተገነባ የሚገኘው ማእከሉ  በመጪው የአውሮፓውያኑ መጋቢት 2018 ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሏል᎓᎓

ማእከሉ ከሰሃራ በታች ያሉ ዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያ፣ ሴራሊዮን ላይበሪያ፣ ጋምቢያ፣ ጋና፣ ኢትዮጵያና ኮትዲቯር የመሳሰሉ አገራትን የሚያገለግል ሲሆን፣  አገልግሎቱን እንዲያገኙ የሚያስችል ደህንነቱ የተጠበቀ የወሊድ ክትትል ለማድርግ ያስችላል ተብሏል᎓᎓

በማዕከሉ አገልግሎት የሚያገኙ ጥንዶች ለወሊድ ክትትል ያወጡት የነበረውን አራት ሺህ ዶላር ወጪ ወደ 980 ዶላር እንደሚቀንሰው ይጠበቃል ሲል የዘገበው አፍሪካ ሪቪው ነው።