በርካታ የአለም ሀገራት የመንግስታቱ ድርጅትን ለማሻሻል ድጋፍ ሰጡ

መስከረም 09፣2010

ከ128 በላይ የሚልቁ የአለም ሀገራት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለማሻሻል የቀረበውን መነሻ ሀሳብ መደገፋቸውን አስታወቁ፡፡

የማሻሻያው ሀሳብም ድርጅቱን ይበልጥ ጠንካራ እና ለህዝቦች ጥያቄ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጽሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በመሩት መድረክ ገልፀዋል፡፡

ድርጅቱ ከሂደት ይልቅ ህዝብ ላይ እንዲያተኩር እንዲሁም ቢሮክራሲን በመቀነስ አቅርቦት ላይ ትኩረት እንዲሰጥ አልሟል ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

በመንግስታቱ ድርጅቱ ስራዎችን የሚያጉዋትቱ አሰራሮችና አደረጃጀቶች እንቅልፍ እንደሚነሳቸው የተናገሩት ዋና ጽሐፊው፤ ይህ በቀጣይ ሊስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡

እኛ የምናገለግላቸውን ሰዎች ለመደገፍ እና የሚደግፉንን ለማገልገል አሰራራችንን ውጤታማና ቀልጣፍ ልናደርግ ይገባል ብለዋል ጉቴሬስ፡፡

የመንግስታቱ ድርጅትን ለማጠናከር የቀረበው ባለ10 ነጥብ የድጋፍ መነሻ ሀሳብ የድርጅቱን አሰራር ቀልጣፋ በማድረግ ይበልጥ ግልጽ ፣ውጤታማና ተጠያቂ እንዲሆን ያስችላል ተብሏል፡፡  

ከቅርብ ወራት ወዲህ በድርጅቱ ባሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች መካከል ያለውን የጾታ ተዋጽኦ ተመጣጣኝ ለማድረግ መታቀዱንም ገልፀዋል ዋና ጽሐፊው፡፡

በአለም ፀጥታና ሰላም ማስከበር ስራዎች ላይም የፀጥታ ችግሮችን ለመከላከልና ለድርድር ትኩረት ይሰጣል ነው የተባለው፡፡

በአለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ የሚፈፀሙ የሴቶች ጾታዊ ትንኮሳና ጥቃቶችን ለማስቀረት እንዲሁም የሰዎች ሰብዓዊ ጥሰትን ለመከላከል የአለም ሀገራት ቁርጠኛ እንዲሆኑ እንደሚሰራም ተነግሯል፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት ለአለም ሀገራት በሚሰጠው የልማት ድጋፍ እ.ኤ.አ በ2030 የተቀመጡ ዘላቂ የልማት ግቦችን በሚያሳካ መልኩ በመቀየስ ሰራዎቹ የተቀናጁና ለህዝብ ትኩረት የሰጡ እንዲሁም ተጠያቂነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ ሊሻሻል እንደሚገባው ተመልክቷል፡፡  

ምንጭ፦ ተመድ