የአፍሪካ ልማት ባንክ ከአፍሪካ ዲያስፖራዎች የሚላክ የውጭ ምንዛሬን ሊያበረታታ ነው

መስከረም 22፣2010

የአፍሪካ ልማት ባንክ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ አፍሪካዊያን/ዲያስፖራዎች/ የሚላክ የውጭ ምንዛሬ ለማጠናከር መወጠኑን አስታወቀ፡፡ 

ውጪ ሀገር ከሚኖሩ ዲያስፖራ አፍሪካዊያን የሚላክ የውጭ ምንዛሬ ይበልጥ ለማሳደግ ባንኩ ከአህጉሪቱ አባል ሀገራት ጋር በመሆን የፋይናንስ ስርዓቱን እያሻሻለ እንደሆነ የባንኩ የምስራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስፈፃሚ ገብሬኤል ንጋቱ በባንኩ የቢዝነስ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል፡፡

ከዲያስፖራ አፍሪካዊያን የሚገኘው የውጭ ምንዛሬም የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠን ያግዛል ተብሏል፡፡

አሁን ላይ ከዲያስፖራ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለአፍሪካ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነም ገልፀዋል ዋና ስራ አስፈፃሚው፡፡

ከአፍሪካ ዲያስፖራዎች የሚላከው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከውጭ ሀገር ግብረሰናይ አካላት ከሚገኝ ድጋፍ እንደሚበልጥም ጠቁመዋል፡፡

ባንኩ የአፍሪካ ዲያስፖራዎች በሀገራቸው መዋእለንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማስቻል የአህጉሪቱ መንግስታት ተገቢ የሆነ ፖሊሲና ህግ እንዲቀርፁ የቴክኒክ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ገልጿል፡፡

የአፍሪካ ዲያስፖራዎች የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገራቸው ሲልኩ አገልግሎቱን ለማግኘት የሚጠየቁት ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ የውጭ ምንዛሬው በሚፈለገው መጠን እዳይላክ እንቅፋት እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

ይህንንም ችግር ለመቅረፍ የአህጉሪቱ መንግስታትና የግል ዘርፉ ከአፍሪካ ዲያስፖራዎች የሚላከው የውጭ ምንዛሬ በአንስተኛ ዋጋ እንዲላክ ዓይነተኛ መፍትኤ ሊያበጁ ይገባል ተብሏል፡፡

ምንጭ፦ ሽንዋ