በአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ለውጥ የግጭት መንስኤ ሊሆን ይችላል፦ተመድ

መስከረም 26፣2010

በአፍሪካ ቀንድ አየር ንብረት ለውጥ እያገረሸ ሲመጣ በግጦሽ መሬትና በውሃ በሚደረግ ሽሚያ ቀጠናው የግጭት ማዕከል ሊሆን እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራም አስጠነቀቀ፡፡ 

የአለም ሙቀት መጨመር በአፍሪካ ቀንድ ለሚከሰቱ የእርስ በርዕስ ግጭቶች፣ ሽብርተኝነትና ስደት ዋና ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ከጉዳዮ ጋር በተያያዘ አንድ ዶክመንተሪ በኬንያ ይፋ ሲሆን የመንግስታቱ ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራም ዋና ስራ አስፈፃሚ ኤሪክ ሶልሄም ተናግረዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ በሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው አገራት የፀጥታ ስጋት ይሆናል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ በአካባቢው ያሉ ማህበረሰቦች በለም መሬት ብግጦሽና በውሃ በሚያደረጉት ሽሚያ የሚነሱ ግጭቶች ሊቀጥሉ ይችላሉ ብለዋል፡፡

በሁለት የእንግሊዝ የፊልም ባለሞያዎች የተዘጋጀው ይህ ዘጋቢ ፊልም የአለም ሙቀት መጨመር በቀጠናው ለሚገኙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የሚፈጥረውን አውዳሚ ተጽእኖ አጎልቶ የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡

የቀጠናው ሀገራት ብሎም ተባባሪ አካላት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚነሱ ግጭቶችን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎችን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተነግሯል፡፡   

በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ማንኛውም ግጭቶች ለመፍታት የሚደረግ ሙከራ የአካባቢ ጥበቃን ማዕከል በማድረግ ሊሰራ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡ 

ከፊታችን ጥቅምት 27 እስከ ህዳር 8 በቦን ከተማ ጀርመን በሚካሄደው አለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ከፀጥታ ጉዳይ ጋር ባለው ግንኙነት ዙሪያ ትኩረት ይሰጠዋል ነው የሚባለው፡፡

በዚህም የአለም ሀገራት ለአለም ሙቀት መጨመር ምክንያት የሆነውን የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ የገቡት ቃል ያድሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመልክቷል፡፡

ምንጭ፦ ሽንዋ