ኢትዮጵያ ከሰሃራ በረሀ በታች ከሚገኙ ሀገራት ፈጣን እድገት ታስመዘግባለች፦ አለም ባንክ

ጥቅምት 2፤2010

ኢትዮጵያ ከሰሃራ  በረሀ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት መካከል ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ቀዳሚ ሀገር እንደምትሆን አለም ባንክ አስታወቀ፡፡

በያዝነው ዓመትም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በ8 ነጥብ 5 በመቶ እንደሚያድግ የተነበየው ደግሞ አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይኤምኤፍ ነው፡፡

ይህም በተመሳሳይ ዓመት 5 በመቶ እድገት ከምታስመዘግበው ኬንያ ጋር ሲነፃፀር የሶስት በመቶ ጭማሪ እንዳለው ተነግሯል፡፡

ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት ኬንያን ከበለጠች በኋላ የምስራቅ አፍሪካ ትላቋ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗ ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጠናው ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ትቀጥላለችም ተብሏል፡፡

በኬንያ ያለው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መቀነሱን ተከትሎ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ቢያገግምም በሀገሪቱ የሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ውጥረት በኢኮኖሚው ላይ የኢንቨስተሮችን እምነት ጥያቄ ውስጥ አስገብቷል ተብሏል፡፡

በቀጣይ ከኢትዮጵያ ቀጥላ ታንዛኒያ የቀጠናው ሁለተኛ ግዙፉ ኢኮኖሚ እንደምትሆን ተመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያ በ2010 በጀት አመት 11 ነጥብ 1 በመቶ እድገት እንደምትስመዘግብ ሰሞኑን የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ መግለፃቸው አይዘነጋም፡፡

ምንጭ፦ ስታንዳርድ ዲጂታል