መንግስታት የአደጋዎች ተጽእኖ ለመቀነስ ሊሰሩ ይገባል፦ አፍሪካ ህብረት

ጥቅምት 3፤2010

የአፍሪካ መንግስታትና ባለድርሻ አካላት በአህጉሩ የሚከሰቱ አደጋዎች የሚያደርሱትን አሉታዊ ተጽእኖ ለመቀነስ ፖሊሲዎችን ሲተገብሩ ብርቱ ጥረት ሊያደረጉ እንደሚገባ አፍሪካ ህብረት አስታወቀ፡፡

ህብረቱ አለም አቀፍ የአደጋ ቅነሳ ቀን በአዲስ አበባ አክብሯል፡፡

ዕለቱ አደጋዎች የሚያደርሱትን ተጽእኖ ለመቀነስ በሚተገበሩ መርሀ-ግብሮች ዙሪያ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ያስችላል ተብሏል፡፡

‹‹የቤት ደህንትን መጠበቅ፣ ተጋላጭነትንና መፈናቀልን መቀነስ›› በሚል መሪ ቃል በታሰበው ቀንም አፍሪካ ለአደጋዎች በእጅጉ ተጋላጭ ሆና እየቀጠለች እንደሆነ ተነግሯል፡፡ 

በእ.ኤ.አ ከ1985 እስከ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ በአፍሪካ በተለያዩ አደጋዎች 210 ሺህ ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ 190 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው መሆኑ ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡

ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን እስከ 22 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ደግሞ እንደዚሁ ማጣቷ ተመልክቷል፡፡

እ.ኤ.አ ከ2000 ወዲህ ከሰሀራ በታች ያሉ ሀገራት በየሳምንቱ በአማካኝ ሁለት አደጋዎች የሚያስተናግዱ ሲሆን በዚህም 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች በየዓመቱ እንደሚጠቁ ተመልክቷል፡፡

ለአብነትም በ2009 ዓ.ም መጨረሻ በሴራሊዮንና በዴሞክራቲክ ኮንጎ በደረሰ የመሬት መንሸራተትና ከባድ የጎርፍ አደጋ በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ የተወሰኑት ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም ነው የተባለው፡፡ 

ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በሰዎች ላይ የሚያደርሱትን አደጋ ለመቀነስ ፖሊሲዎችን በተገቢው መንገድ መተግበር እንደሚገባ በአፍሪካ ህብረት የማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር አሚራ ኢል ፋዲል ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ሱዳንና ኡጋንዳ በአፍሪካ በአደጋ ተጋላጭነት ቀዳሚ የሆኑ ሀገሮች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

ባለፉት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ አስደናቂ የኢኮኖሚ እድገት ብታስመዘግብም የተፈጥሮ አደጋ ለሀገሪቱ ከፍተኛ ፈተና እንደሆነ የብሔራዊ አደጋ ክስተት ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችም በድርቅ አደጋ ተጠቅተዋል ብለዋል፡፡

ምንጭ፦ ሽንዋ