የግብፅና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች የህዳሴ ግድብን ጎበኙ

ጥቅምት7 ፤2010

የግብጽ እና ሱዳን የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚንስትሮች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ  ግድብን ዛሬ ጉባ ተገኝተው ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚንስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ፣ የሱዳኑ አቻቸው ሙአተዝ ሙሳና የግብፁ ውሃ ሃብትና መስኖ ሚንስትር መሃመድ አብደል አቲ ናቸው ግድቡን በጋራ የጎበኙት።

የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ የግድቡን አጠቀላይ ግንባታ ለሚንስትሮቹ አስጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የውሃ ሚንስትሮች ከዚህ በፊት ግድቡን በተናጠል የጎበኙት ቢሆንም በአንድ ላይ ግድቡን ሲጎበኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚስቴር አስታውቋል።

ጉብኝቱን ተከትሎም ነገ በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ 16ኛው የሶስትዮሽ ብሄራዊ ኮሚቴ ስብሰባ ይካሄዳል፡፡

በስብሰባው ሚንስትሮቹ በህዳሴው ግድብ ወቅታዊ ጉዳዮች በተለይም በዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን፣ እንዲጠኑ ብሎ በሰጠው ምክረ ሃሳብ መሰረት የሚጠኑትን ሁለት ጥናቶች በተመለከተ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በናትናኤል ፀጋዬ