ደኢህዴን የሕዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች እየገመገመ ነው

ጥቅምት 7፣2010

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ የጥልቅ ተሀድሶውን ተከትሎ የሕዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ያሉበትን ደረጃ በሰፊው እየገመገመ ነው፡፡

በተለይም በተሀድሶው ተለይተው የወጡ ችግሮችን ፈጥኖ ከማረም አንፃር በአጭርና መካከለኛ ጊዜ እልባት ማግኘት የሚገባቸውን ጉዳዮች በሕዝባዊ ውግንና ቃኝቶ ከማረምና በአጠቃላይ የሕዝቡን እርካታ ደረጃ በደረጀ በራሱ በሕዝቡ የተደራጀ ተሳትፎ እያረጋገጡ ከመሄድ አንፃር የተመዘገቡ ስኬቶችንና ጉድለቶችን በዝርዝር በመገምገም ላይ ነው፡፡

ድርጅታዊ ኮንፈረንሱ የአመራሩና የአባሉ ፖለቲካዊና ድርጅታዊ አቅም እንዲጎለብት ወቅቱ እየጠየቀ ያለውን ብቃትና ዝግጁነት እንዲላበስ በማድረግ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ የመላውን ሕዝብ ተጠቃሚነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲያረጋግጥ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየመከረ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተለይም በጥልቅ ተሀድሶው ወቅት ከሕዝብ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን መፍታት ጊዜ የማይሰጠው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚፈቱበትን አግባብና ፍጥነት እየገመገመ ነው፡፡

ክልሉ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንዲሁም የኃይማኖት ብዝሀነትን የሚያስተናግድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በብዝሀነት ውስጥ ያለው አንድነት ለልማት ተግባራት አጋዥነቱን ከዚህ ቀደም ከነበረው በላይ በፍጥነት የሚሰራበት ምቹ ሁኔታዎች ላይም እየተወያየ ነው፡፡

ሁሉንም የልማት ተግባራት በተደራጀ የልማት ሠራዊት ከመፈፀም አንፃር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ቢመጣም አሁንም ቀሪ ተግባራት ያሉ በመሆኑ ሊፈቱ የሚችሉበትን መንገድ በዝርዝር ገምግሟል፡፡

ሀገሪቱ ፈጣንና ተከታታይ ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገበች በመሆኗ ይህንኑ ቀጣይነትና ዘለቄታነቱን በማረጋገጥ ረገድ አመራሩ የሚጠበቅበትን የመሪነት ሚናውና ያለበትን ደረጃ ይገመግማል፡፡

ድርጅታዊ ኮንፈረንሱ ከጥልቅ ተሀድሶው ወዲህ ባለፈው አንድ አመት በክልሉ የተመዘገቡ ስኬታማ ተግባራትን በማስቀጠል ያጋጠሙና የተስተዋሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ በሚከናወኑ ተግባራት ላይም እየመከረ ነው፡፡

ዘገባው የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ነው፡፡