የአፍሪካ ልማት ባንክ የአህጉሪቱን የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ያለመ ስልጠና መስጠት ጀመረ

ጥቅምት 08፣2010

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያና ለሌሎች የአፍሪካ አገራት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪያቸውን  ለማሳደግ የሚያስችል ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡

በኢትዮጵያ የተጀመረው ስልጠና በኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያና በኮትዲቫዋር እንደሚሰጥም ተነግሯል፡፡  

ስልጠናው የአፍሪካ ሀገሮች በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ በአለም አቀፍ ገበያ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግና ተወዳዳሪ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ፋሽን ዲዛይነሮች ማህበር አባላት፣ የፋሽን ልብሶች ስራ ፈጣሪዎችና ተማሪዎች በስልጠናው ላይ በመካፈል ላይ መሆናቸውን ባንኩ በድረ ገፁ ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡

ባንኩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባዘጋጀው ስልጠናው በአፍሪካ የሚመረቱ የአልባሳት ምርቶች እንዴት በራሳቸው መለያ(ብራንድ) ፋሽን ሆነው በአለም አቀፍ ገበያ ተቀባይነት እንደሚያገኙ የተሻለ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንደሚረዳም ተመልክቷል፡፡    

አሁን ላይ በዘርፉ ምርት ለአለም ከፍተኛ አቅርቦት በሚሰጠው በኢስያ ያለው የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት  የማምረቻ ወጪ ከፍተኛ እየሆነ ይገኛል፡፡

በአንፃሩ በአፍሪካ ያለው የዘርፉ  የማምረቻ ወጪ ዝቅተኛ መሆን በአለም ገበያ ምርቱን በተሻለ ዋጋ ለማቅረብ እድል ይሰጣል ተብሏል፡፡

በተለይ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ በኢትዮጵያ ያለው ሰፊ እድል ሀገሪቷን በአለም አቀፍ ገበያ የተሻለ የፋሽን ምርቶች በማቅረብ ረገድ አዲስ ምንጭ  እየሆነች መምጣቷን ዘገባው አመልክቷል፡፡

በዚህም በአለም አቀፍ ገበያ ኢትዮጵያ የዘርፉ ምርቶች ተወዳዳሪ እየሆኑ እንደሚገኙ ተጠቅሷል፡፡

በወጪ ንግድ አፍሪካ በዓመት 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የአልባሳት ምርቶች ለአለም ገበያ እንደምታቀርብ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ምንጭ፦ አፍሪካ ልማት ባንክ