የአፍሪካ ከተሞች ፈጣን እድገት ለኢንደስትሪ መስፋፋት ይረዳል- ተመድ

ጥቅምት 10፤2010

በአፍሪካ የሚታየው ፈጣን የከተሞች  እድገት  ለኢንዱስትሪዎች  መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተመድ አስታወቀ᎓᎓

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት እንደገለጸው አፍሪካ ከከተሞች እድገት ጋር ተመጣጣኝና ትክክለኛ የሆነ ፖሊሲ ተቀርፆ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ከኢንዱስትሪ እድገት አህጉሪቱ ተጠቃሚ ትሆናለች፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ምክትል ዋና ጸሃፊ ጂዮቫኒ ቢሃ በጊጋሊ የ2017 የኢኮኖሚ ሪፖርት በቀረበበት ወቅት እንደገለጹት የአፍሪካ ከተሞች እድገት የተመራው የግብርና ምርት በማሳደግ ወይም ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ ግብአቶችን በማምረት እይደለም ብለዋል᎓᎓

በአንጻሩ እንደ አገልግሎት ያሉ የኢኮኖሚ ክፍሎችን በማሳደግና  የአገልግሎት አሰጣጥን በማስቀደም ነው የከተሞች እድገት ሊመጣ የቻለው ብለዋል᎓᎓

በአህጉሪቱ እድገትን ለማምጣትና ድህነትን ለመቀነስ የአፍሪካ ሃገራት ክህሎት የሚጠይቁ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚችሉ የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ ይኖርባቸዋል ተብሏል፡፡

ይህንን ተግባራዊ ካደረጉ በኢኮኖሚ እድገታቸው ላይ ተጨባጭ የሆነ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት እንደማይቸግራቸው ሪፖርት አብራርቷል፡፡

በ2035 የአህጉሪቱ ግማሽ የሚሆነው ህዝብ በከተማ እንደሚኖር ይገመታል᎓᎓ ይህ ሁኔታ ደግሞ በከተሜነትና ኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሄ ለማፈላለግ ይረዳል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት አመታት የአምራች ኢንደስትሪው በአፍሪካ እየቀነሰ የመጣ ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ የአገልግሎት ዘርፉ እያደገ መምጣቱን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

ይሁንና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የምስራቃዊ አፍሪካ ሀገራት የአምራች ኢንደስትሪው በተሻለ መልኩ እያደገ መምጣቱ ተነግሯል፡፡

ምንጭ፡ ተመድ