የምዕራባዊያን ባለሀብቶችንና ፖለቲከኞችን የታክስ ቅሌት ያጋለጠ ሰነድ ይፋ ሆነ

ጥቅምት 27፣2010

በአለም የበርካታ ሀያላን ባለሀብቶችንና ፖለቲከኞችን የታክስና የገንዘብ ዝውውር ቅሌትን ያጋለጠ ድብቅ ሰነድ ይፋ ሆነ፡፡

‹‹ፓራዳይዝ ፔፐር›› ተብሎ የሚጠራው ይህ አለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኝነት ግኝት በአለም የሚገኙ ስመጥር ባለሀብቶች፤ ኩባንያዎች፣ የመንግስታት መሪዎችና ሌሎች ሀያልን ግለሰቦች ድንበር ተሻጋሪ እንቅስቃሴያቸውንና ፍላጎታቸውን ያጋለጠ ሰነድ ነው ተብሏል፡፡

13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰነዶችን የያዘው ‹‹ፓራዳይዝ ፔፐር›› በዋናነት ታዋቂ ግለሰቦች፣ ኩባንያዎችና ፖለቲከኞች ባለአደራ ድርጅቶች፣ ግብረሰናይ ተቋማትና ሼል የተባለ የነዳጅ ኩባንያን በመጠቀም የሚያገኙትን ገንዘብ እንዴት ከአገራት ግብር ስርዓእንደሚያሸሹ አልያም የውል ስምምነቶችን በሚስጢር እንደሚፈጽሙ የሚያጋልጥ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በዚህ የግብር ማጭበርበር የተሳተፉ ግለሰቦችና ኩባንያዎች በሀገራቸው የሚጣልባቸውን ከፍተኛ ግብር ለመሸሽ በዋናነት ንብረታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ትርፋቸውን ዝቅተኛ ግብር በሚያስከፍሉ ሀገሮች ተቀማጭ እንደሚያደርጉ ተነግሯል፡፡ 

በእነዚህ የግብር ማጭበርበር ቅሌት ውስጥ ስማቸው ከተነሳ ግለሰቦች መካከል የወቅቱ የብሪታኒያ ንግስት አንዷ ሆነዋል፡፡

ንግስቲቷ በውጭ ሀገር በሚገኙ ንብረቷ ላይ በድብቅ 13 ሚሊዮን ዶላር መዋለንዋይ ታፈሳለች ተብሏል፡፡

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የወቅቱ የኢኮኖሚ ሚንስትርም በዚህ ሚስጥራዊ ሰነድ ውስጥ የድብቅ ኢንቨስትመንት እንደሚያካሂዱ ተደርሶበታል፡፡

አብዛኞቹ የገንዘብ ዝውውሮች በህጋዊ መንገድ ስለሚፈፀሙ ጥፋታቸው በውል ሳይታወቅ ቆይቶ እንደነበር ተነግሯል፡፡

ሰነዱን ይፋ ያደረገው ‹‹አፕልባይ›› የተሰኘ የህግ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ ሲሆን፤ ዝርዝር ሰነዱን ከኩባያው ተቀብለው ምርመራ ያደረጉት ደግሞ በ67 ሀገራት ባሉ ቁጥራቸው 100 በሚጠጋ የሚዲያ አካላት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በሚዲያ አካላት ምርመራ የተደረገበት ይህ የቅሌት ሰነድ የህዝቦችን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያለመ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ምንጭ፦ ቢቢሲ