በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ

ህዳር 1፤2010

በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት በኢጋድ አማካይነት ለተጀመረው ጥረት ፍሬያማነት የትሮይካ አባል ሀገራት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ብሪታኒያ አሜሪካና ኖርዌይን ካካተተው የትሮይካ አባል ሀገራት ልዑካን ቡድን ጋር በደቡብ ሱዳን ዙሪያ ወይይት አድርገዋል፡፡

ሚኒስትሩ በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት የሀገሪቱን መንግሥት ጨምሮ ከተቀናቃኝ ኃይሎች ጋር ባለፉት ወራት የተካሄዱ ውይይቶች ስኬታማ እንደነበሩ አብራርተውላቸዋል፡፡

ተፋላሚ ወገኖቹ የተኩስ አቁም ለማድረግና የሰላም ስምምነቱን በአፋጣኝ ተግባራዊ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸውም ገልፀዋል፡፡

የትሮይካ አባል ሀገራት በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ አባላት በበኩላቸው ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት እያደረገች ያለውን አስተዋፅኦ አድንቀው ኢጋድ በሀገሪቱ ሰላም ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ መናገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ተናግረዋል፡፡

ዘገባው የሪፖርተራችን አለማየሁ ታደለ ነው፡፡