አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶችን ያለመሸራረፍ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች

ህዳር 08፣2010

አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶችን ያለመሸራረፍ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ኢትዮጵያ 47 ታዳጊ አገራትን በመወከል ጥሪ አቀረበች፡፡

በጀርመን ቦን እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር  ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ 47 ታዳጊ አገራትን በመወከል ነው የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶች አለመተግበር እንዳሳሳባት የገለፀችው፡፡

በፊጂ ፕሬዝዳንትነት በሚመራው በዚሁ  ኮፕ 23  ተብሎ በሚጠራው የቦኑ  የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የአካባቢ ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚንስትሩ ገመዶ ዳሌ (ዶ/ር) እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አረንጓዴ ኢኮኖሚን በራሳቸው ጥረት እየገነቡ ያሉ አገራት በፅኑ ሊደገፉ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ የካርብን ጋዝ  ልቀትን በ64 በመቶ ለመቀነስ ብሄራዊ ዋነኛ አጀንዳ አድርጋ እየሰራች ነው ያሉት ሚንስትሩ፣ ያደጉም ሆነ ታዳጊ አገራት ለፓሪሱ አየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ትግባራ በጋራ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሚንስትሩ ገመዶ ዳሌ (ዶ/ር) እንዳሉት የቦኑ ኮፕ 23 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ  ከመቼውም ጊዜ በላቀ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋን ተገንዝበን እርምጃ የምንወስድበት ትክክለኛው ወቅት አሁን ነው ብለዋል፡፡በተለይም ከባለፈው ዓመት ወዲህ የታየው ከባድ ድርቅ፣ሰደድ እሳትና ከባድ የሙቀት ማዕበል እንዲሁም  በቅርቡ በአሜሪካ ተከስቶ የነበረው ውሽንፍር አዘል ከባድ  አውሎ ነፍስና ያስከተለው ውድመት ተጨባጭ ማስረጃዎች መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ታዳጊ አገራት ለነዚህ የአየር ንብረት ለውጥ ክስተቶች ምንም ያበረከቱት አስተዋፅኦ ሳይኖር  ግንባር ቀደም ተጠቂ መሆናቸውን በመድረኩ ላይ ተናግረዋል፡፡ይህም አገራቱ ህዝባቸውን ከድህነት ለማላቀቅ የያዙትን ጥረትና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በታዳጊ አገራቱ ላይ   ተግዳሮቱን የከፋ እንዳደረገው ኢትዮጵያ አስገንዝባለች፡፡

ወሳኝ አገራት ከዚህ ቀደም የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶችን ለመተግበር ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ባለማሳየታቸው ታዳጊ አገራቱ እየተጎዱ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

እ.ኤ.አ በ2020 የበካይ ጋዝ ልቀትን ከ1.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች ለመወሰን የተገባው ስምምነትን እውን ከማድረግ የተለየ አማራጭ ባመኖሩ፣ ታዳጊ አገራቱ ለጥረቱ ቁርጠኞች መሆናቸውን ኢትዮጵያ አቋሟን አንፀባርቃለች፡፡በዚህም አለም አቀፉ ማህበረሰቡ የሚጠበቅበትን ድርሻ ሊወጣ የሚያስችለውን ኃላፊነት እንዲወስድም ጠይቀዋል፡፡

የአየርን ንብረት ለውጥ ባደረሰው ኪሰራና መቋቋሚያ መንገዶች ላይ የተገቡ ስምምነቶች ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበሩና ለታዳጊ አገራቱ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲሰጥም ኢትዮጵያ መጠየቋን የአካባቢ፣ደንናየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር  ከጀርመን ቦን ለኢቢሲ ያደረሰው መረጃ ያመለክታል፡፡