ኡጋንዳ በሱዳን ለሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ሀይል ልምምድ ወታደሮቿን ላከች

ህዳር 13 ፣2010

ኡጋንዳ በሱዳን በሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ሀይል የሰላም ማስከበር ጦር ልምምድ 106 ወታደሮቿን ላከች፡፡

ለሁለት ሳምንት በሚቆየው በዚህ የጦር ልምምድ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ10 የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ ወታደሮች ተሳታፊ እንደሚሆኑ የኡጋንዳ ጦር ሰራዊት ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጀነራል ሪቻርድ ካሬሚር ተናግረዋል፡፡

‹‹ማሻሪኪ ሳላም II›› ተብሎ የሚጠራው በዚህ የጦር ልምምድ የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ሀይል በሰላም ማስከበር፣ ሽብርተኝነትና ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በመዋጋት ረገድ ብቃቱን ለመጨመር ታስቦ የሚካሄድ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በጦር ልምምዱ ላይም ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ጂቡቲ፣ ብሩንዲ፣ ኮሞሮስ፣ ሶማሊያና ሲሸልስ ተሳታፊ ይሆኑበታል ተብሏል፡፡

ሀገሮቹ በጦር ልምምዱ ሽብርተኝነትን በመዋጋት፣ መረጃ በማሰባሰብና በሌሎችም መስኮች በርካታ ተሞክሮዎችን ይለዋወጡበታል ብለዋል ጀነራሉ፡፡  

የጦር ልምምዱ በዋናነት በቀጠናው ለሚፈጠሩ ቀውሶች የተጠንቀቅ ሀይሉን ምላሽ የመስጠት አቅሙን በመፈተሽ ዝግጁነቱን ለማጠናከር ታስቦ የሚካሄድ እንደሆነም ተነግረዋል፡፡ 

የቻይና፣ አውሮፓ ህብረትና የአሜሪካ የጦር ተወካዮች በወታደራዊ ስልጠናው እንደሚታደሙ ታውቋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2004 የተቋቋመው የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ሀይል በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን ፈጣን እርምጃ የሚወስድና ከአምስቱ የአፍሪካ ተጠንቀቅ ሀይል አንዱ ነው፡፡

ምንጭ፦ ሽንዋ