ኢትዮጵያ የዓለም ታላላቅ ስም ያላቸው የጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾችን እየሳበች ነው-ሮይተርስ

ህዳር 13፡2010

ኢትዮጵያ የዓለም ታላላቅ ስም ያላቸው የጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራች ድርጅቶችን በመሳብ በዘርፉ ከፍተኛ ተስፋ እንዳላት ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

አገሪቱ በዘርፉ የረጅም ጊዜ ልምድ ካላቸው አገራት ጋር ስትወዳደር በዋጋው ቅናሽ ያለው የኢንቨስትመንት አማራጭ በማቅረብ በአልባሳትና ፋሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ታላላቅ ስም ያላቸውን እንደ "ኤች ኤንድ ኤም" እና "ጋፕ" ያሉ ድርጅቶችን ለመሳብ ችላለች ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ ኢንቨስትመትን ለመሳብ ካቀረበችው አማራጭ በተጨማሪም በቅርቡ ስራ የሚጀምረው የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመርም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ዘገባው አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ መሰረት በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ አገሪቱ እ.አ.አ 2013 ያገኘችው 4.5 ቢሊዮን ብር ገቢ በ2016/2017 ወደ 36.8 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ መቻሏም ተጠቅሷል፡፡

ዘንድሮ በኢትዮጵያ ስራ ይጀምራሉ ተብለው ከሚጠበቁት የዓለማችን ታላላቅ ድርጅቶች ውስጥ የአሜሪካው "የካልቪን ኬሊን" እና "የቶሚ" ብራንዶችን የሚያመርተው "ፒቪኤች" እንዲሁም መቀመጫውን በዱባይ ያደረገው "የሌቪስ"፣ "ዛራ" እና "አንደር አርመር" አምራቹ "ቬሎሲቲ አፓሬልዝ" በተጨማሪም "የጆርጂዮ አርማኒ" እና "ሁጎ ቦስ" አምራቹ የቻይናው "ጃንግሱ ሰንሻይን ግሩፕ" ይገኙበታል፡፡

አገሪቱ በዘርፉ የምታደርገው የእድገት ግስጋሴ ግን በጥጥ ምርት ጥራት ጉድለት፣ በአሰራር እንግልት መብዛት /ቢሮክራሲ/ እና የሎጂቲክስ አቅርቦት ችግሮች ምክንያት እንዳይገታ አሁንም ሰፊ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው በዘገባው ተጠቁሟል፡፡

በዓለም ባንክ መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ እኤአ በ2015 ከዘርፉ 115 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች።

ምንጭ፡- ሮይተርስ