የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ማንጋግዋ ፕሬዝዳንት ለመሆን ቃለ መሃላ ሊፈጽሙ ነው

ህዳር 13፡2010

የቀድሞ የዚምባቤ ምክትል ፕሬዝዳንት ኢመርሰን ማንጋግዋ ሮበርት ሙጋቤን በመተካት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ለመሆን የፊታችን አርብ ቃለ መሀላ ሊፈጽሙ ነው።

ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በዚምባብዊ እንዲኖር በሚል ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁት የ93 ዓመቱ ሮበርት ሙጋቤ ከሁለት ሳምንት በፊት ምክትል ፕሬዝዳንቱን ከስልጣናቸው አበረው ነበር፡፡

ይህም እርምጃ የሀገሪቱ ገዥ ፓርቲ የሆነው ‹‹ዛኑ ፒኤፍ›› እንዲሁም ጦር ሰራዊቱ ጣልቃ እንዲገቡ በማስገደድ ሮበርት ሙጋቤ ከመንበረ ስልጣናቸው እንዲወገዱ ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡

ሮበርት ሙጋቤ የህዝብ ይሁንታ ተነፍጓቸው በከፍተኛ ጫና ስልጣናቸውን ከለቀቁ በሃላም የቀድሞ የዙምባቤ ምክትል ፕሬዝዳንት ማንጋግዋ የሀገሪቱን ኢኮኖሚና ዲሞክራሲ እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሳሉ ተብለው ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡

ለዚህም ሲባል የቀድሞ የነፃነት ታጋይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ማንጋግዋ እ.ኤ.አ በወረሀ መስከረም 2018 የሀገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡

የ75 ዓመት እድሜ ያላቸው የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ማንጋግዋ በሀገሪቱ ጦር ሰራዊት ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለቸው ይነገራል፡፡

በፊታችን ዕለተ አርብም የቀድሞ የዙምባቤ ምክትል ፕሬዝዳንት ኢመርሰን ማንጋግዋ ቃለ መዓላቸውን በመስጠት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት እንደሚሆኑ ተመልክቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሮበርት ሙጋቤ ከስልጣናቸው ለመልቀቅ የወሰኑትን ውሳኔ አፍሪካ ህብረት እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡

ምንጭ፦ አልጃዚራና ቢቢሲ