ሴቶች የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ህዳር 14፣2010

ሴቶች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት እንዲሁም የውሃ መስኖና ተፈጥሮ ሃብትን ጨምሮ የስድስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ዳይሬክቶሬቶችን የአንደኛ ሩብ አመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

በቋሚ ኮሚቴው የተገመገሙት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ሴቶችን ከማብቃትና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመከላከል ጅምር ስራዎች ቢሰሩም የታሰበውን ያክል ለመፈጸም ግን ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቁሟል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በሀገሪቱ ብዛት ያላቸው ፋብሪካዎች ቢኖሩም የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ክፍተት እንዳለባቸው ገልጿል፡፡

በመሆኑም በቀጣይ ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ለይቶ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

በሌላ በኩል ተቋማቱ ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመከላከል፣ ሴቶችን ለማብቃትና ኤች.አይ.ቪ ኤድስ በደማቸው የሚገኝ ወላጅ አልባ ህጻናትን እንዲሁም አረጋውያንን ለመርዳት የተሻለ ስራ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል፡፡