የሚዲያ ምክር ቤት ህጋዊ ሰውነት ያለማግኘት በመረጃ ተደራሽነት ላይ ችግር መፍጠሩ ተጠቆመ

ህዳር 14፣2010

የሚዲያ ምክር ቤት ህጋዊ ሰውነት ያለማግኘትና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ማስተግበርያ ደንቦች ያለመውጣት በጋዜጠኖች መብት ጥበቃም ሆነ በመረጃ ተደራሽነት ላይ ችግር መፍጠሩ ተጠቆመ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንግስት  ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት የ2010 ዕቅድና የሩብ ዓመት አፈፃፀም ገምግሟል፡፡

በሚዲያው አካባቢ የሚፈጠሩ ብልሽቶችን በአስተዳደራዊ እርምጃ ከመፍታት ይልቅ ጋዜጠኛው በምክር ቤት ተደራጅቶ ደንብ በማውጣት ጋዜጠኛውን የሚያርምበት አሰራር እንደሚዘረጋ ፅህፈት ቤቱ አመላክቷል፡፡የሚዲያ ምክር ቤቱም ባለፈው ዓመት ተመስርቷል፡፡

ይሁን እንጂ የበጎ አድራጎት ኤጀንሲ የተቋቋመው ምክር ቤት የሚድያ ባለቤቶች እንጂ የጋዜጠኛው ባለመሆኑ ለመመዝገብ ህጉ አይፈቅድም በማለቱ ምክርቤቱ አለመመዝገቡን ጽ/ቤቱ ገልጧል፡፡

የመረጃ ነፃነት አዋጅ ትግበራ፣ ምስጥራዊና ምስጥራዊ ያልሆኑ የመረጃ ምድቦችን የሚለይና የመረጃ ክፍያ ተመንን የሚወስኑ ደንቦች እየተዘጋጁ ነው ተብሏል፡፡

ደንቦቹ በወቅቱ ተጠናቀው የዜጎች የመረጃ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ ጽሕፈት ቤ ጠንክሮ እንዲሰራ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

ዘገባው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ነው፡፡