ዶናልድ ትራምፕ 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኑ

ጥቅምት 30፣ 2009

የሪፐብሊካኑ ተወካይ ዶናልድ ትራምፕ በ2016 የአሜሪካ ምርጫ ይሁንታ ተሰጥቷቸው 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡

ተቀናቃኛቸው ሄላሪ ክሊንተን በውጤቱ እንኳን ድስ አላችሁ ማለታቸውን ትራምፕ ተናግረዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ከ538 የምርጫ ጣቢያዎች 288 ድምጾችን አግኝቷል፡፡ በምርጫው ፕሬዝዳንት ለመሆን 270 ድምፅ ማግኘት በቂ ነው፡፡

የመጀመሪያዋ የአሜሪካ ሴት ፕሬዝዳንት ለመሆን ተቃርበው የነበሩት ዲሞክራቷ ሄላሪ ክሊንተን በመጨረሻ ሽንፈት ገጥሟቸዋል፡፡

ሄላሪ ክሊንተን 215 ደምፆችን ብቻ ነው ማግኘት የቻሉት፡፡

የሪፐብሊካን ፓርቲ በአሜሪካው የህዝብ መወሰኛ ምክር ቤትም/ሴኔት/ ብልጫ ወሰዷዋል፡፡

በኒው ዮርክ የተሰባሰቡት የትራምፕ ደጋፊዎች በውጤቱ የደስታ ስካር ላይ ሲገኙ፣ በዚያው በኒው ዮርክ ሌላኛው ጫፍ የተሰባሰቡት የሄላሪ ደጋፊዎች በሀዘን ተበትነዋል፡፡

የሄላሪ የምርጫ አስተባባሪም ደጋፊዎቻቸውን እረፍት አድርጉ ብቻ በማለት የሀዘን ድባቡን እንዲበተን አድርገዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ትልቁን ድል አስመልክተው ተስብስበው ለሚጠብቋቸው ደጋፊዎች ንግግር ሲያደርጉ የመረጧቸውን ካመሰገኑ በኋላ አሁን እንደ አሜሪካ በጋራ የምንስራበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡

ቃል እገባላችኋለሁ እንደመረጣችሁኝ አላሳፍራችሁም ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ የትራምፕ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ማይክ ፔንስም ሀገሬን በምክትል ፕሬዝዳንትነት ለማገልገል በመቻሌ ክብር ይሰማኛል ብለዋል፡፡

በምርጫው ቅስቀሳ ሄላሪ ክሊንተን ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ተጠቅመዋል፡፡ ቱጃሩ ትራምፕ በበኩላቸው በ8 መቶ ሚሊዮን ዶላር ምርጫውን መርቷል፡፡

ምርጫውን ተከትሎ የኤሲያ ገበያ መቀዛቀዝ አሳይቷል፡፡ የትራምፕ መመረጥ ያሰጋው  የሜክሲኮ መንግስት ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ሰዓት ቀጥሯል፡፡

በምርጫው የተወዳዳሪዎች አወዛጋቢ ጉዳዮች ፡-

የዲሞክራቶች ፓርቲ ተወካይ ሄላሪ ክሊንተን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ያለ ሀገሪቱ ደህንነት ተቋም ጥበቃ የተለዋወጧቸው ከ65ሺህ በላይ የኢሜል መልዕክቶች በምርጫው ሂደት አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል፡፡

በሄላሪ ቤተሰብ የሚመራው የእርዳታ ድርጅት  ከዓላማው ውጭ ነው መባሉም ሌላው የሄላሪ ክሊንተን  የምርጫ ጥላ ነበር፡፡

ተቀናቃኛቸው የሪፐብሊካኑ ተወካይ ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ዘረኛ ባህሪ ማሳየታቸው፣ በንግድ ስራቸው ተገቢውን ክፍያ ለባለሙያዎች አለመክፈላቸው፣ በተደጋጋሚ በኪሳራ መመታታቸው፣ ሙስሊሞች ወደ ሀገራቸው እንዳይገቡ እግዳ ለመጣል እና የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸውን ስድተኞች ከሀገሪቱ ለማስወጣት ማሰባቸው በብዙዎቹ መራጮች ዘንድ ፊት እንዲዞርባቸው አድርጓቸዋል፡፡

የሁለቱን ችግሮች በራሱ ሚዛን የለካው የአሜሪካ ህዝብ የትራምፕን መሪነት መርጧል፡፡