በእስራኤል የተነሳው ሰደድ እሳት በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያቸው አፈናቀለ

ህዳር 16፡2009

በእስራኤል 3ኛዋ ትልቅ ከተማ ሃይፋ በተነሳው ሰደድ እሳት ምክንያት በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን 80 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎችም ከአካባቢው እንዲለቁ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶዋቸዋል፡፡

ለሁለት ወራት የቆየውን ደረቅ የአየር ሁኔታ ተከትሎ በከተማዋ ሰሜናዊ ክፍል የሚነፍሰው ጠንካራ  ነፋስ እሳቱን አባብሶታል፡፡

የሰደድ እሳቱ አደጋ በእየሩሳሌምና በዌስት ባንክ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችንም ስጋት ላይ ጥሏል፡፡

አደጋው ባስከተለው ጭስ ሳቢያ ከ13ዐ የሚበልጡ ሰዎች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን በከተማዋ አቅራቢያ የነበሩ ሁለት ማረሚያ ቤቶችም ወድመዋል ተብሏል፡፡

ቤቶችና መኪኖች ተቃጥለዋል 3ዐዐ ያህል ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀላቸው ሲገለጽ የከተማዋ አቅራቢያ አካባቢዎችም ሌሊቱን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደተቋረጠባቸው ነው የተገለጸው፡፡

የእስራኤል ፖሊስ በአንዳንድ ቦታዎች ሆነ ተብሎ እሳት እንደተነሳ የሚጠቁሙ መረጃዎ አሉኝ ያለ ሲሆን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ  እንደዚ ያሉ ጥቃቶች ከሽብር አይተናነሱም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ በእንደዚህ  አይነት የሽብር ተግባር ላይ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ ከባድ ቅጣት ይጠብቀዋል ብለዋል፡፡

ቆጵሮስ፣ሩስያ፣ጣሊያን፣ክሮሺያና ግሪክ እሳቱን ለማጥፋት አውሮኘላንን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለዕርዳታ ወደ ስፍራው ልከዋል፡፡

ቢቢሲ በዘገባው እንዳሰፈረው በፈረንጆቹ 2010 በደቡባዊ ሃይፋ በምትገኘው ሞንት ካርሜል በደረሰ የእሳት ቃጠሎ 42 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ምንጭ፡ ቢቢሲ