አሜሪካ በሱዳን ላይ ለ20 ዓመት ጥላው የቆየውን ማዕቀብ አነሳች

ጥር  08፣2009

የአሜሪካ መንግስት በሱዳን ላይ ላለፉት 20 ዓመታት ጥሎት የቆየውን ምጣኔ ሀብት  ማዕቀብ ማንሳቱን አስታወቀ፡፡

የተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት  በከፊል ማዕቀቡን ያነሳው በዋናነት በንግድ፣ ፋይናንስና በቋሚ ንብረቶች ላይ ሲሆን፤ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት እንደሚያሻሽለውም ተነግሯል፡፡

ለሱዳን ያልተረጋጋ ኢኮኖሚ ገፀበረከት እንደሆነ የተነገረለት ይህ የአሜሪካ ውሳኔ እውን የሆነውም የሱዳን መንግስት በሀገሪቱ ባሉ ግጭቶች እረቀ ሰላም ለማውረድ ባለፉት ስድስት ወራት ባሳየው ጥረት ነው ተብሏል፡፡

የአሁኑ የአሜሪካ ውሳኔ የተላለፈውም ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በሱዳን ላይ ተጥሎ የከረመውን በርካታ ማዕቀቦችን በቋሚነት ለመሰረዝ በማህደር ላይ ፊርማቸውን ካኖሩ በሃላ እንደሆነ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

የማዕቀቡን መነሳት ተከትሎም ሱዳን ከአሜሪካ ምርትና አገልግሎቶችን ማስገባት ትችላለች፣ እንዲሁም በአሜሪካ ተይዘው የቆዩ የሱዳን ቋሚ ንብረቶች ይለቀቃሉ ነው የተባለው፡፡   

 በተጨማሪም የነዳጅና የጋዝ ምርቷን ወደ አሜሪካ ለመላክ በር የከፈተላት እንደሆነ ዘገባው ጠቅሷል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት አሜሪካ ከሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል በሁለቱ ሀገሮች ያለውን ያለመተማመን ውስንነት ለመቅረፍ ባሳዩት ፍላጎት የአሁኑ ማዕቀብ እንዲነሳ  አድርገጎታል ይላሉ   ተንታኞች ፡፡

የሱዳን መንግስትም  ውሳኔውን መቀበሉ ታውቋል፡፡

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጋሪብአላህ ከዲር በበኩላቸው የአሁኑ የአሜሪካ ውሳኔ በጋራ ጥረት ከተካሄደ ግልጽ ውይይት በሃላ የተፈጠረና የሀገሮቹን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሻሻል ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  

ይሁን እንጂ አሜሪካ የሱዳን መንግስት ሽብርተኝነትን ተቋማዊ በሆነ አሰራር ይደግፋል በሚል የጣለውን ማዕቀብ እንዲሁም ከዳርፉር ግጭት ጋር በተያያዘ የተጣሉ የመሳሪያ ሽያጭና ቁጥጥሮች እንደማይነሱ ዘገባው አመልክቷል፡፡